82 - The Cleaving - Al-'Infiţār
:1
ሰማይ በተሰነጠቀች ጊዜ፤
:2
ከዋክብትም ተበታትነው በወደቁ ጊዜ፤
:3
ባሕሮችም በተከፈቱና በተደበላለቁ ጊዜ፤
:4
መቃብሮችም በተገለባበጡና (ሙታን) በተነሱ ጊዜ፤
:5
ማንኛይቱም ነፍስ ያስቀደመችውንና ያቆየችውን ታውቃለች፡፡
:6
አንተ ሰው ሆይ! በቸሩ ጌታህ ምን አታለለህ?
:7
በዚያ በፈጠረህ አካለ ሙሉም ባደረገህ ባስተካከለህም፡፡
:8
በማንኛውም በሻው ቅርፅ በገጣጠመህ (ጌታህ ምን አታለለህ)፡፡
:9
ተከልከሉ፤ በእውነቱ በፍርዱ ቀን ታስተባብላላችሁ፡፡
:10
በእናንተ ላይ ተጠባባቂዎች ያሉባችሁ፤ ስትኾኑ፤
:11
የተከበሩ ጸሐፊዎች የኾኑ፤ (ተጠባባቂዎች)፡፡
:12
የምትሠሩትን ሁሉ የሚያውቁ፡፡
:13
እውነተኞቹ ምእምናን በእርግጥ በገነት ውስጥ ናቸው፡፡
:14
ከሓዲዎቹም በእርግጥ በገሀነም ውስጥ ናቸው፡፡
:15
በፍርዱ ቀን ይገቧታል፡፡
:16
እነርሱም ከርሷ ራቂዎች አይደሉም፡፡
:17
የፍርድ ቀን ምን እንደኾነ ምን አሳወቀህ?
:18
ከዚያም የፍርዱ ቀን ምን እንደኾነ ምን አሳወቀህ?
:19
(እርሱ) ማንኛይቱም ነፍስ ለሌላይቱ ነፍስ ምንም ማድረግን የማትችልበት ቀን ነው፡፡ ነገሩም ሁሉ በዚያ ቀን ለአላህ ብቻ ነው፡፡