ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

81 - The Overthrowing - At-Takwīr

:1

ፀሐይ በተጠቀለለች ጊዜ፤

:2

ከዋክብትም በረገፉ ጊዜ፤

:3

ተራራዎችም በተነዱ ጊዜ፤

:4

የዐሥር ወር እርጉዞች ግመሎችም (ያለጠባቂ) በተተዉ ጊዜ፤

:5

እንስሳትም ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜ፤

:6

ባሕሮችም በተቃጠሉ ጊዜ፤

:7

ነፍሶችም (በየአካሎቻቸው) በተቆራኙ ጊዜ፤

:8

በሕይወቷ የተቀበረችውም ሴት ልጅ በተጠየቀች ጊዜ፤

:9

በምን ወንጀል እንደ ተገደለች፤

:10

ጽሑፎችም በተዘረጉ ጊዜ፤

:11

ሰማይም በተገሸለጠች ጊዜ፤

:12

ገሀነምም በተነደደች ጊዜ፤

:13

ገነትም በተቀረበች ጊዜ፤

:14

ነፍስ ሁሉ (ከሥራ) ያቀረበችውን ታውቃለች፤

:15

ተመላሾችም በኾኑት (ዐዋድያት) እምላለሁ፡፡

:16

ኺያጆች ገቢዎች በኾኑት (ከዋክብት)፡፡

:17

በሌሊቱም (ጨለማውን) በጠነሰሰ ጊዜ፤

:18

በንጋቱም (በብርሃን) በተነፈሰ ጊዜ፤ (እምላለሁ)፡፡

:19

እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡

:20

የኀይል ባለቤት በዙፋኑ ባለ ቤት ዘንድ ባለሟል የኾነ፡፡

:21

በዚያ ስፍራ ትእዛዙ ተሰሚ፤ ታማኝ የኾነ (መልክተኛ ቃል) ነው፡፡

:22

ነቢያችሁም በፍጹም ዕብድ አይደለም፡፡

:23

በግልጹ አድማስም በእርግጥ አይቶታል፡፡

:24

እርሱም በሩቁ ወሬ ላይ ሰሳች (ንፉግ) አይደለም፡፡

:25

እርሱም (ቁርኣን) የእርጉም ሰይጣን ቃል አይደለም፡፡

:26

ታዲያ ወዴት ትኼዳላችሁ?

:27

እርሱ የዓለማት መገሠጫ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡

:28

ከናንተ ቀጥተኛ መኾንን ለሻ ሰው (መገሰጫ ነው)፡፡

:29

የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም፡፡