ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

69 - The Reality - Al-Ĥāqqah

:1

እውነትን አረጋጋጪቱ (ትንሣኤ)፡፡

:2

አረጋጋጪቱም (እርሷ) ምንድን ናት!

:3

አረጋጋጪቱም ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ?

:4

ሰሙድና ዓድ በቆርቋሪይቱ (ትንሣኤ) አስተባበሉ፡፡

:5

ሠሙድማ ወሰን በሌላት ጩኸት ተጠፋ፤ (ተወደሙ)፡፡

:6

ዓድማ በኀይል በምትንሻሻ ብርቱ ነፋስ ተጠፉ፡፡

:7

ተከታታይ በኾኑ ሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልቶች ውስጥ በእነርሱ ላይ ለቀቃት፡፡ ሕዝቦቹንም፤ በውስጧ የተጣሉ ኾነው ልክ ክፍት የኾኑ የዘንባባ ግንዶች መስለው ታያቸዋለህ፡፡

:8

ለእነርሱም ቀሪን ታያለህን?

:9

ፈርዖን ከበፊቱ የነበሩትም ሰዎች ተገልባጮቹም (ከተሞች) በኀጢአት (ሥራዎች) መጡ፡፡

:10

የጌታቸውንም መልእክተኛ ትዕዛዝ ጣሱ፡፡ የበረታችንም አያያዝ ያዛቸው፡፡

:11

እኛ ውሃው ባየለ ጊዜ በተንሻላይቱ ታንኳ ውስጥ ጫንናችሁ፡፡

:12

ለእናንተ መገሰጫ ልናደርጋት አጥኒ የኾነችም ጆሮ ታጠናት ዘንድ፡፡

:13

በቀንዱም አንዲት መንነፋት በተነፋች ጊዜ፡፡

:14

ምድርና ጋራዎችም (ከስፍራቸው) በተነሱና አንዲትን መሰባበር በተሰባበሩ ጊዜ፡፡

:15

በዚያ ቀን ኋኝቱ (ትንሣኤ) ትኾናለች፡፡

:16

ሰማይም ትቀደዳለች፡፡ ስለዚህ እርሷ በዚያ ቀን ደካማ ናት፡፡

:17

መላእክትም በየጫፎችዋ ላይ ይኾናሉ፡፡ የጌታህንም ዐርሽ በዚያ ቀን ስምንት መላእክት ከበላያቸው ይሸከማሉ፡፡

:18

በዚያ ቀን ከእናንተ ተደባቂ (ነገሮች) የማይደበቁ ሲኾኑ ትቅቀረባላችሁ፡፡

:19

መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ (ለጓደኞቹ) «እንኩ፤ መጽሐፌን አንብቡ» ይላል፡፡

:20

«እኔ ምርመራየን የምገናኝ መኾኔን አረጋገጥኩ፤» (ተዘጋጀሁም ይላል)፡፡

:21

እርሱም በተወደደች ኑሮ ውሰጥ ይኾናል፡፡

:22

በከፍተኛይቱ ገነት ውስጥ፡፡

:23

ፍሬዎችዋ ቅርቦች የኾኑ፡፡

:24

በአለፉት ቀናት ውስጥ (በምድረ ዓለም) ባስቀደማችሁት ምክንያት ብሉ፤ ጠጡም፤ (ይባላሉ)፡፡

:25

መጽሐፉንም በግራው የተሰጠማ «ዋ ጥፋቴ! ምነው መጽሐፌን ባልተሰጠሁ» ይላል፡፡

:26

«ምርመራየንም ምን እንደኾነ ባላወቅኩ፡፡

:27

«እርሷ (ሞት ሕይወቴን) ምነው ፈጻሚ በኾነች፡፡

:28

«ገንዘቤ ከእኔ ምንንም አላብቃቃኝ፤ (አልጠቀመኝም)፡፡

:29

«ኀይሌ ከእኔ ላይ ጠፋ» (ይላል)፡፡

:30

«ያዙት፤ እሰሩትም፡፡

:31

«ከዚያም በእሳት ውሰጥ አግቡት፡፡

:32

«ከዚያም ርዝመቷ ሰባ ክንድ በኾነች ሰንሰለት ውስጥ አግቡት፡፡»

:33

እርሱ ታላቅ በኾነው አላህ አያምንም ነበርና፡፡

:34

ድኾችንም በማብላት ላይ አያግባባም ነበርና፡፡

:35

ለእርሱም ዛሬ እዚህ ዘመድ የለውም፡፡

:36

ምግብም ከእሳት ሰዎች ቁስል እጣቢ (እዥ) በስተቀር የለውም፡፡

:37

ኀጢኣተኞች እንጅ ሌላ አይበላውም፤ (ይባላል)፡፡

:38

በምታዩትም ነገር እምላለሁ፡፡

:39

በማታዩትም ነገር፡፡

:40

እርሱ (ቁርኣን) የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው፡፡

:41

እርሱም የባለቅኔ ቃል (ግጥም) አይደለም፡፡ ጥቂትን ብቻ ታምናላችሁ፡፡

:42

የጠንቋይም ቃል አይደለም፡፡ ጥቂትን ብቻ ታስታውሳላችሁ፡፡

:43

ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡

:44

በእኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ፤

:45

በኀይል በያዝነው ነበር፡፡

:46

ከዚያም ከእርሱ የልቡን ሥር (የተንጠለጠለበትን ጅማት) በቆረጥን ነበር፡፡

:47

ከእናንተም ውስጥ ከእርሱ ላይ ከልካዮች ምንም አይኖሩም፡፡

:48

እርሱም (ቁርኣን) ለጥንቁቆቹ መገሠጫ ነው፡፡

:49

እኛም ከእናንተ ውስጥ አስተባባዮች መኖራቸውን በእርግጥ እናውቃለን፡፡

:50

እርሱም (ቁርኣን) በከሓዲዎቹ ላይ ጸጸት ነው፡፡

:51

እርሱም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡

:52

የታላቁን ጌታህንም ስም አወድስ፡፡