ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

68 - The Pen - Al-Qalam

:1

ነ.(ኑን)፤ በብርእ እምላለሁ በዚያም (መልአኮች) በሚጽፉት፡፡

:2

አንተ በጌታህ ጸጋ የተጎናጸፍክ ስትኾን ዕብድ አይደለህም፡፡

:3

ላንተም (ከጌታህ) የማይቋረጥ ዋጋ በእርግጥ አልለህ፡፡

:4

አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡

:5

ወደፊትም ታያለህ፤ ያያሉም፡፡

:6

ዕብደት በማንኛችሁ እንዳልለ፡፡

:7

ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የተሳሳተውን ሰው ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ተመሪዎቹን ዐዋቂ ነው፡፡

:8

ለአስተባባዮችም አትታዝዙ፡፡

:9

ብትመሳሰላቸውና ቢመሳሰሉህ ተመኙ፡፡

:10

ወራዳንም ሁሉ አትታዘዝ፡፡

:11

ሰውን አነዋሪንና በማሳበቅ ኼያጅን፡፡

:12

ለበጎ ነገር በጣም ከልካይን፣ ወሰን አላፊን፣ ኃጢአተኛን፤

:13

ልበ ደረቅን፣ ከዚህ በኋላ ዲቃላን (ሁሉ አትታዘዝ)፡፡

:14

የገንዘብና የልጆች ባለቤት በመኾኑ (ያስተባብላል)፡፡

:15

በእርሱ ላይ አንቀጾቻችን በሚነበቡ ጊዜ «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናቸው» ይላል፡፡

:16

በአፍንጫው ላይ በእርግጥ (የሚነወርበት) ምልክት እናደርግበታለን፡፡

:17

እኛ የአትክልቲቱን ባለቤቶቸ እንደ ሞከርን (የመካን ሰዎች) ሞከርናቸው፡፡ ማልደው (ፍሬዋን) ሊለቅሟት በማሉ ጊዜ፡፡

:18

(በመሓላቸው) አያስቀሩምም፡፡

:19

እነርሱ የተኙ ኾነውም ሳሉ ከጌታህ የኾነ ዟሪ በእርሷ ላይ ዞረባት፡፡

:20

እንደ ሌሊት ጨለማም ኾና አነጋች፤ (ከሰለች)፡፡

:21

ያነጉም ኾነው ተጠራሩ፡፡

:22

«ቆራጮች እንደ ኾናችሁ በእርሻቸሁ ላይ ማልዱ» በማለት፡፡

:23

እነርሱ የሚንሾካሾኩ ኾነው ኼዱም፡፡

:24

ዛሬ በእናንተ ላይ ድኻ እንዳይገባት በማለት፡፡

:25

(ድኾችን) በመከልከልም ላይ (በሐሳባቸው) ቻዮች ኾነው ማለዱ፡፡

:26

(ተቃጥላ) ባዩዋትም ጊዜ «እኛ በእርግጥ ተሳሳቾች ነን» አሉ፡፡

:27

«ይልቁንም እኛ የተከለከልን ነን» አሉ፡፡

:28

ትክክለኛቸው «ለእናንተ አላህን ለምን አታጠሩም አላልኳችሁምን?» አላቸው፡፡

:29

«ጌታችን ጥራት ይገባው፡፡ እኛ በዳዮች ነበርን፤» አሉ፡፡

:30

የሚወቃቀሱም ኾነው ከፊሎቻቸው በከፊሉ ላይ መጡ፡፡

:31

«ዋ ጥፋታችን! እኛ ድንበር አላፊዎች ነበርን፤» አሉ፡፡

:32

«ጌታችን ከእርሷ የተሻለን (አትክልት) ሊለውጠን ይከጀላል፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ከጃዮች ነን፤» (አሉ)፡፡

:33

ቅጣቱ እንደዚሁ ነው፡፡ የመጨረሻይቱም ዓለም ቅጣት ታላቅ ነው፡፡ የሚያውቁት በኾኑ ኖሮ (በተጠነቀቁ ነበር)፡፡

:34

ለጥንቁቆቹ በጌታቸው ዘንድ መጠቀሚያ ገነቶች አሏቸው፡፡

:35

ሙስሊሞቹን እንደ ከሓዲዎች እናደርጋለን?

:36

ለእናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ፡፡

:37

በእውነቱ ለእናንተ በእርሱ የምታጠኑበት መጽሐፍ አላችሁን?

:38

በውስጡ ለእናንተ የምትመርጡት አላችሁ (የሚል)

:39

ወይስ ለእናንተ የምትፈርዱት አላችሁ በማለት (ቃል ኪዳን የገባንላችሁ) እስከ ትንሣኤ ቀን ደራሽ የኾኑ መሓላዎች ለእናንተ በእኛ ላይ አሏችሁን?

:40

በዚህ ማንኛቸው ተያያዥ እንደ ኾነ ጠይቃቸው፡፡

:41

ወይስ ለእነርሱ (በፍርዳቸው ተስማሚ) «ተጋሪዎች» አሏቸውን? እውነተኞችም እንደኾኑ «ተጋሪዎቻቸውን» ያምጡ፡፡

:42

ባት የሚገለጥበትን (ከሓዲዎች) ወደ መስገድም የሚጥጠሩበትንና የማይችሉበት ቀን (አስታውስ)፡፡

:43

ዓይኖቻቸው የፈሩ ውርደት የምትሸፍናቸው ሲኾኑ፤ (ወደ ስግደት የሚጠሩበትን)፤ እነርሱም (በምድረ ዓለም) ደህና ኾነው ሳሉ ወደ ስግደት በእርግጥ ይጠሩ ነበሩ፡፡

:44

በዚህም ንግግር ከሚያስተባብሉት ሰዎች ጋር ተዎኝ፡፡ (እነርሱን እኔ እበቃሃለሁ)፡፡ ከማያውቁት ስፍራ አዘናግተን እንይዛቸዋለን፡፡

:45

እነርሱንም አዘገያለሁ፡፡ ዘዴዬ ብርቱ ነውና፡፡

:46

በእውነቱ ዋጋን ትጠይቃቸዋለህን? ስለዚህ እነርሱ ከዕዳ የተከበዱ ናቸውን?

:47

ወይስ እነርሱ ዘንድ የሩቁ ምስጢር ዕውቀት አልለን? ስለዚህ እነርሱ ይጽፋሉን?

:48

ለጌታህም ፍርድ ታገሥ፤ (በመበሳጨትና ባለ መታገሥ) እንደ ዓሣው ባለቤትም (እንደ ዮናስ) አትኹን፡፡ እርሱ በጭንቀት የተመላ ኾኖ (ጌታውን) በተጣራ ጊዜ፡፡

:49

ከጌታው የኾነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ በምድረ በዳ ተወቃሽ ኾኖ በተጣለ ነበር፡፡

:50

ጌታውም (በነቢይነት) መረጠው፡፡ ከደጋጎቹም አደረገው፡፡

:51

እነሆ እነዚያም የካዱት ሰዎች ቁርኣኑን በሰሙ ጊዜ በዓይኖቻቸው ሊጥሉህ (ሊያጠፉህ) ይቀርባሉ፡፡ «እርሱም በእርግጥ ዕብድ ነው» ይላሉ፡፡

:52

ግን እርሱ (ቁርኣን) ለዓለማት መገሰጫ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡