ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

67 - The Sovereignty - Al-Mulk

:1

ያ ንግሥና በእጁ የኾነው አምላክ ችሮታው በዛ፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

:2

ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፡፡ እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው፡፡

:3

ያ ሰባትን ሰማያት የተነባበሩ ኾነው የፈጠረ ነው፡፡ በአልረሕማን አፈጣጠር ውስጥ ምንም መዛነፍን አታይም፡፡ ዓይንህንም መልስ፡፡ «ከስንጥቆች አንዳችን ታያለህን?»

:4

ከዚያም ብዙ ጊዜ ዓይንህን መላልስ፡፡ ዓይንህ ተዋርዶ እርሱም የደከመ ኾኖ ወዳንተ ይመለሳል፡፡

:5

ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በከዋክብት) አጌጥናት፡፡ ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት፡፡ ለእነርሱም (ለሰይጣኖች) የእሳትን ቅጣት አዘጋጀን፡፡

:6

ለእነዚያም በጌታቸው ለካዱት የገሀነም ቅጣት አልላቸው፡፡ መመለሻይቱም ከፋች!

:7

በውስጧ በተጣሉ ጊዜ፤ እርሷ የምትፈላ ስትኾን ለእርሷ (እንደ አህያ) ማናፋትን ይሰማሉ፡፡

:8

ከቁጭትዋ የተነሳ ልትቆራረጥ ትቀርባለች፡፡ በውስጧ ጭፍሮች በተጣሉ ቁጥር ዘበኞችዋ «አስፈራሪ (ነቢይ) አልመጣችሁምን?» በማለት ይጠይቋቸዋል፡፡

:9

«አይደለም በእርግጥ አስፈራሪ መጥቶናል፡፡ አስተባበልንም፡፡ አላህም ምንንም አላወረደ እናንተ (አውርዷል ስትሉ) በትልቅ ስህተት ውስጥ እንጅ አይደላችሁም አልን» ይላሉ፡፡

:10

«የምንሰማ ወይም የምናስብ በነበርንም ኖሮ በነዳጅ እሳት ጓዶች ውስጥ ባልኾን ነበር» ይላሉ፡፡

:11

በኀጢኣታቸውም ያምናሉ ለእሳት ጓዶችም (ከእዝነት) መራቅ ተገባቸው፡፡

:12

እነዚያ ጌታቸውን በሩቁ የሚፈሩ ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አልላቸው፡፡

:13

(ሰዎች ሆይ!) ቃላችሁንም መስጥሩ፡፡ ወይም በእርሱ ጩሁ፡፡ እርሱ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

:14

የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀት ረቂቁ፣ ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን?

:15

እርሱ ያ ምድርን ለእናንተ የተገራች ያደረገላችሁ ነው፡፡ በጋራዎችዋና በመንገዶችዋም ኺዱ፡፡፡ ከሲሳዩም ብሉ፡፡ (ኋላ) መመለሻውም ወደእርሱ ብቻ ነው፡፡

:16

በሰማይ ውስጥ ያለን (አላህ) በእናንተ ምድርን ቢደረባባችሁ ወዲያውም እርሷ የምታረገርግ ብትኾን ትተማመናላችሁን? (አትፈሩምን?)

:17

ወይም በሰማይ ውስጥ ያለን በእናንተ ላይ ጠጠርን ያዘለች ነፋስን ቢልክባችሁ ትተማመናላችሁን? (አትፈሩምን?) ማስጠንቀቄም እንዴት እንደኾነ ወደፊት ታውቃላችሁ፡፡

:18

እነዚያም ከእነርሱ በፊት የነበሩት በእርግጥ አስተባበሉ፡፡ ጥላቻዬም እንዴት ነበር!

:19

ወደ አእዋፍ ከበላያቸው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ተንሳፋፊዎች የሚሰበሰቡም ሲኾኑ አላዩምን? ከአልረሕማን በቀር (ባየር ላይ) የሚይዛቸው የለም፡፡ እርሱ በነገሩ ሁሉ ተመልካች ነው፡፡

:20

በእውነቱ ያ እርሱ ከአልረሕማን ሌላ የሚረዳችሁ ለእናንተ የኾነ ሰራዊት ማነው? ከሓዲዎች በመታለል ውስጥ እንጅ በሌላ ላይ አይደሉም፡፡

:21

ወይም ሲሳዩን ቢይዝባችሁ ያ ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማነው? በእውነቱ እነርሱ በሞገድና በመደንበር ውስጥ ችክ አሉ፡፡

:22

በፊቱ ላይ ተደፍቶ የሚኼድ ሰው ይበልጥ የቀና ነውን? ወይስ በቀጥተኛ መንገድ ላይ ተስተካክሎ የሚኼድ?

:23

«እርሱ ያ የፈጠራችሁ ለእናንተም መስሚያና ማያዎችን፣ ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው፡፡ ጥቂትንም አታመስግኑም» በላቸው፡፡

:24

«እርሱ ያ በምድር ላይ የበተናቸሁ ነው፡፡ ወደእርሱም ትሰበሰባላችሁ» በላቸው፡፡

:25

«እውነተኞችም እንደኾናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡

:26

«ዕውቀቱ አላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም» በላቸው፡፡

:27

(ቅጣቱን) ቅርብ ኾኖ ባዩትም ጊዜ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ፊቶች ይክከፋሉ፡፡ «ይህ ያ በእርሱ ትከራከሩበት የነበራችሁት ነው» ይባላሉም፡፡

:28

«አያችሁን? አላህ ቢገድለኝ ከእኔ ጋር ያሉትንም (እንደዚሁ) ወይም (በማቆየት) ቢያዝንልን ከሓዲዎችን ከአሳማሚ ቅጣት የሚያድን ማን ነው?» በላቸው፡፡

:29

«እርሱ (እመኑበት የምላችሁ) አልረሕማን ነው፡፡ (እኛ) በእርሱ አመንን፡፡ በርሱም ላይ ተጠጋን፡፡ ወደ ፊትም በግልጽ መሳሳት ውስጥ የኾነው እርሱ ማን አንደ ኾነ በእርግጥ ታውቃላችሁ» በላቸው፡፡

:30

«አያችሁን? ውሃችሁ ሠራጊ ቢኾን ፈሳሺን ውሃ የሚያመጣላቸሁ ማን ነው?» በላቸው፡፡ (አላህ የዓለማት ጌታ ያመጣዋል)፡፡