ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

70 - The Ascending Stairways - Al-Ma`ārij

:1

ወዳቂ ከኾነው ቅጣት ጠያቂ ጠየቀ፡፡

:2

በከሓዲዎች ላይ (ወዳቂ ከኾነው) ለእርሱ መላሽ የለውም፡፡

:3

የ(ሰማያት) መሰላሎች ባለቤት ከኾነው አላህ (መላሽ የለውም)፡፡

:4

መላእክቱና መንፈሱም ልኩ አምሳ ሺሕ ዓመት በኾነ ቀን ውስጥ ወደእርሱ ያርጋሉ፤ (ይወጣሉ)፡፡

:5

መልካምንም ትዕግስት ታገሥ፡፡

:6

እነርሱ (ያንን ቀን) ሩቅ አድርገው ያዩታል፡፡

:7

እኛም ቅርብ ኾኖ እናየዋለን፡፡

:8

ሰማይ እንደ ዘይት አተላ በምትኾንበት ቀን፡፡

:9

ጋራዎችም በተለያዩ ቀለማት እንደ ተነከረ ሱፍ (ነፋስ እንደሚያበረው) በሚኾኑበት ቀን፡፡

:10

ዘመድም ዘመድን በማይጠይቅበት ቀን፤ (መላሽ የለውም)፡፡

:11

(ዘመዶቻቸውን) ያዩዋቸዋል፡፡ አመጸኛው ከዚያ ቀን ስቃይ (ነፍሱን) በልጆቹ ሊበዥ ይመኛል፡፡

:12

በሚስቱም በወንድሙም፡፡

:13

በዚያችም በምታስጠጋው ጎሳው፡፡

:14

በምድርም ላይ ባለው ሁሉ (ሊበዥ) ከዚያም ሊያድነው (ይመኛል)፡፡

:15

ይተው! እርሷ (እሳቲቱ) ለዟ ናት፡፡

:16

የራስን ቅል ቆዳ የምትሞሽልቅ ስትኾን፡፡

:17

(ከእምነት) የዞረንና የሸሸን ሰው (ወደእርሷ) ትጠራለች፡፡

:18

ገንዘብን የሰበሰበንና (ዘካውን ሳይሰጥ) የቆጠረንም፤ (ትጠራለች)፡፡

:19

ሰው ቅጠ ቢስ ኾኖ ተፈጠረ፡፡

:20

ክፉ ነገር ባገኘው ጊዜ ብስጪተኛ፡፡

:21

መልካምም ነገር (ድሎት) ባገኘ ጊዜ ከልካይ (ኾኖ ተፈጠረ)፡፡

:22

ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ፡፡

:23

እነዚያ እነርሱ በስግደታቸው ላይ ዘውታሪዎች የኾኑት፡፡

:24

እነዚያም በገንዘቦቻቸው ላይ የታወቀ መብት ያለባቸው የኾኑት፡፡

:25

ለለማኝ ከልመና ለሚከለከልም (መብት ያለባቸው የኾኑት)፡፡

:26

እነዚያም በፍርዱ ቀን እውነት የሚሉት (የሚያረጋግጡት)፡፡

:27

እነዚያም እነርሱ ከጌታቸው ቅጣት ፈሪዎች የኾኑት፡፡

:28

የጌታቸው ቅጣት (መምጣቱ) የማያስተማምን ነውና፡፡

:29

እነዚያም እነርሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የኾኑት፡፡

:30

በሚስቶቻቸው ወይም እጆቻቸው በያዙዋቸው (ባሪያዎች) ላይ ሲቀር፡፡ እነርሱ (በእነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና፡፡

:31

ከዚያም ወዲያ የፈለገ ሰው እነዚያ እነሱ ድንበር አላፊዎች ናቸው፡፡

:32

እነዚያም እነርሱ አደራዎቻቸውንና ቃል ኪዳናቸውን ጠባቂዎች የኾኑት፡፡

:33

እነዚያም እነርሱ በምስክርነታቸው ትክክለኞች የኾኑት፡፡

:34

እነዚያም እነርሱ በሶላቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁት፡፡

:35

እነዚህ (ከዚህ በላይ የተወሱት ሁሉ) በገነቶች ውስጥ የሚከበሩ ናቸው፡፡

:36

ለእነዚያም ለካዱት ወደ አንተ በኩል አንገቶቻቸውን መዝዘው የሚያተኩሩት ምን አላቸው?

:37

ከቀኝና ከግራ ክፍልፍል ጭፍሮች ሲኾኑ፡፡

:38

ከእነርሱ እያንዳንዱ ሰው የጸጋይቱን ገነት መግባትን ይከጅላልን?

:39

ይከልከል፤ እኛ ከሚያውቁት ነገር (ከፍቶት ጠብታ) ፈጠርናቸው፡፡

:40

በምሥራቆችና በምዕራቦችም ጌታ እምላለሁ፡፡ እኛ በእርግጥ ቻዮች ነን፡፡

:41

ከእነርሱ የተሻለን በመለወጥ ላይ፡፡ እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም፡፡

:42

ያንንም የሚስፈራሩበትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው፡፡ ይዋኙ ይጫወቱም፡፡

:43

ወደ ጣዖቶች እንደሚሽቀዳደሙ ኾነው ከመቃብሮቻቸው ፈጥነው የሚወጡበትን ቀን (እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው)፡፡

:44

ዓይኖቻቸው ያፈሩ ኾነው ውርደት ትሸፍናቸዋለች፡፡ ይህ ቀን ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ነው፡፡