ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

50 - The Letter "Qaf" - Qāf

:1

ቀ (ቃፍ) በተከበረው ቁርኣን እምላለሁ (በሙሐመድ አላመኑም)፡፡

:2

ይልቁንም ከነሱ ጎሳ የኾነ አስፈራሪ ስለ መጣላቸው ተደነቁ፡፡ ከሓዲዎቹም «ይህ አስደናቂ ነገር ነው» አሉ፡፡

:3

«በሞትንና ዐፈር በኾን ጊዜ (እንመለሳለን?) ይህ ሩቅ የኾነ መመለስ ነው፤» (አሉ)፡፡

:4

ከእነርሱ (አካል) ምድር የምታጎድለውን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ እኛም ዘንድ ጠባቂ መጽሐፍ አልለ፡፡

:5

(አልተመለከቱም)፡፡ ይልቁንም በቁርኣን በመጣላቸው ጊዜ አስተባበሉ፡፡ እነርሱም በተማታ ነገር ውሰጥ ናቸው፡፡

:6

ወደ ሰማይም ከበላያቸው ስትኾን ለእርሷ ምንም ቀዳዳዎች የሌሏት ኾና እንዴት እንደ ገነባናትና (በከዋክብት) እንዳጌጥናት አልተመለከቱምን?

:7

ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ በውስጧም ከሚያስደስት ዓይነት ሁሉ አበቀልን፡፡

:8

(ይህንን ያደረግነው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ነው፡፡

:9

ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፡፡ በእርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን፡፡

:10

ዘምባባንም ረዣዢም ለእርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትኾን (አበቀልን)፡፡

:11

ለባሮቹ ሲሳይ ትኾን ዘንድ (አዘጋጀናት)፡፡ በእርሱም የሞተችን አገር ሕያው አደረግንበት፡፡ (ከመቃብር) መውጣትም እንደዚሁ ነው፡፡

:12

ከእነርሱ በፊት የኑሕ ሕዝቦችና የረሰስ ሰዎች፤ ሰሙድም አስተባበሉ፡፡

:13

ዓድም ፈርዖንም፤ የሉጥ ወንድሞችም፤

:14

የአይከት ሰዎችም የቱብበዕ ሕዝቦችም ሁሉም መልከተኞቹን አስተባበሉ፡፡ ዛቻዬም ተረጋገጠባቸው፡፡

:15

በፊተኛው መፍጠር ደከምን? በእውነቱ እነርሱ ከአዲስ መፍጠር በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡

:16

ሰውንም ነፍሱ (በሐሳቡ) የምታጫውተውን የምናውቅ ስንኾን በእርግጥ ፈጠርነው፤ እኛም ከደም ጋኑ ጅማት ይበልጥ ወደርሱ ቅርብ ነን፡፡

:17

ሁለቱ ቃል ተቀባዮች (መላእክት) ከቀኝና ከግራ ተቀማጮች ኾነው በሚቀበሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:18

ከቃል ምንም አይናገርም በአጠገቡ ተጠባባቂና ዝግጁ የኾኑ (መላእክት) ያሉበት ቢኾን እንጅ፡፡

:19

የሞትም መከራ እውነቱን ነገር ታመጣለች፡፡ (ሰው ሆይ)፡- «ይህ ያ ከርሱ ትሸሸው የነበርከው ነው» (ይባላል)፡፡

:20

በቀንዱም ውስጥ ይንነፋል፡፡ ያ (ቀን) የዛቻው (መፈጸሚያ) ቀን ነው፡፡

:21

ነፍስም ሁሉ ከእርሷ ጋር ነጂና መስካሪ ያለባት ኾና ትመጣለች፡፡

:22

«ከዚህ ነገር በእርግጥ በዝንጋቴ ውስጥ ነበርክ፡፡ ሺፋንህንም ካንተ ላይ ገለጥንልህ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ዓይንህ ስለታም ነው» (ይባላል)፡፡

:23

ቁራኛውም (መልአክ) «ይህ ያ እኔ ዘንድ ያለው ቀራቢ ነው» ይላል፡፡

:24

«ሞገደኛ ከሓዲን ሁሉ በገሀነም ውስጥ ጣሉ፡፡»

:25

«ለበጎ ሥራ ከልካይ፣ በዳይ፣ ተጠራጣሪ የኾነን ሁሉ፤» (ጣሉ)፡፡

:26

«ያንን ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ ያደረገውን በብርቱ ቅጣት ውስጥ ጣሉት፤» (ይባላል)፡፡

:27

ቁራኛው (ሰይጣን) «ጌታችን ሆይ! እኔ አላሳሳትኩትም፡፡ ግን (ራሱ) በሩቅ ስሕተት ውስጥ ነበር» ይላል፡፡

:28

(አላህ) «ወደእናንተ ዛቻን በእርግጥ ያስቀደምኩ ስኾን እኔ ዘንድ አትጨቃጨቁ» ይላቸዋል፡፡

:29

«ቃሉ እኔ ዘንድ አይለወጥም፡፡ እኔም ለባሮቼ ፈጽሞ በዳይ አይደለሁም» (ይላቸዋል)፡፡

:30

ለገሀነም «ሞላሽን? የምንልበትንና ጭማሪ አለን? የምትልበትን ቀን» (አስጠንቅቃቸው)፡፡

:31

ገነትም አላህን ለፈሩት እሩቅ ባልኾነ ስፍራ ትቅቀረባለች፡፡

:32

«ይህ ወደ አላህ ተመላሽና (ሕግጋቱን) ጠባቂ ለኾነ ሁሉ የተቀጠራችሁት ነው» (ይባላሉ)፡፡

:33

«አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራና በንጹሕ ልብ ለመጣ» (ትቅቀረባለች)፡፡

:34

«በሰላም ግቧት ይህ የመዘውተሪያ ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡

:35

ለነርሱ በውስጧ ሲኾኑ የሚሹት ሁሉ አልላቸው፡፡ እኛም ዘንድ ጭማሪ አልለ፡፡

:36

ከእነርሱም (ከቁረይሾች) በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን እነርሱ በኀያልነት ከእነርሱ ይበልጥ የበረቱ የኾኑትን (ማምለጫ ፍለጋ) በየአገሮቹም የመረመሩትን አጥፍተናል፡፡ ማምለጫ አለን?

:37

በዚህ ውሰጥ ለእርሱ ልብ ላለው ወይም እርሱ (በልቡ) የተጣደ ኾኖ (ወደሚነበብለት) ጆሮውን ለጣለ ሰው ግሳጼ አለበት፡፡

:38

ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ድካምም ምንም አልነካንም፡፡

:39

በሚሉትም ላይ ታገሥ፤ ጌታህንም ከማመስገን ጋር ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ከመግባቷም በፊት አወድሰው፡፡

:40

ከሌሊቱም አወድሰው ከስግደቶችም በኋላዎች (አወድሰው)፡፡

:41

(የሚነገርህን) አዳምጥም፡፡ ጠሪው ከቅርብ ስፍራ በሚጠራበት ቀን (ከመቃብራቸው ይወጣሉ)፡፡

:42

ጩኸቲቱን በእውነት የሚሰሙበት ቀን ያ (ከመቃብር) የመውጫው ቀን ነው፡፡

:43

እኛ እኛው ሕያው እናደርጋለን፡፡ እንገድላለንም፡፡ መመለሻም ወደእኛ ብቻ ነው፡፡

:44

የሚፈጥኑ ኾነው ምድር ከእነርሱ ላይ የምትሰነጣጠቅበት ቀን (የመውጫው ቀን ነው)፡፡ ይህ በእኛ ላይ ገር የኾነ መሰብሰብ ነው፡፡

:45

እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂ ነን፡፡ አንተም በእነርሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም፡፡ ስለዚህ ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ፡፡