ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

62 - The Congregation, Friday - Al-Jumu`ah

:1

በሰማያት ያለው በምድርም ያለው ሁሉ ለአላህ ንጉሥ፣ ቅዱስ፣ አሸናፊ፣ ጥበበኛ ለኾነው ያሞግሳል፡፡

:2

እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርኣንን) በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከእነርሱው ውስጥ የላከ ነው፡፡ እነርሱም ከእርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ፡፡

:3

ከነሱም ሌሎች ገና ያልተጠጉዋቸው በኾኑት ላይ (የላከው ነው)፡፡ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡

:4

ይህ የአላህ ችሮታ ነው፡፡ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፡፡ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡

:5

የእነዚያ ተውራትን የተጫኑትና ከዚያም ያልተሸከሟት (ያልሠሩባት) ሰዎች ምሳሌ መጽሐፎችን እንደሚሸከም አህያ ብጤ ነው፡፡ የእነዚያ በአላህ አንቀጾች ያስተባበሉት ሕዝቦች ምሳሌ ከፋ፡፡ አላህም በዳዮችን ሕዝቦች አይመራም፡፡

:6

«እናንተ አይሁዳውያን የኾናችሁ ሆይ! ከሰው ሁሉ በስተቀር እናንተ ብቻ ለአላህ ወዳጆች ነን ብትሉ እውነተኞች እንደኾናችሁ ሞትን ተመኙ» በላቸው፡፡

:7

እጆቻቸውም ባስቀደሙት ኃጢአት ምክንያት በፍጹም አይመኙትም፡፡ አላህም በዳዮቹን ዐዋቂ ነው፡፡

:8

«ያ ከእርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ወደ ኾነው ጌታ ትመለሳላችሁ፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል» በላቸው፡፡

:9

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በዐርብ ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት ኺዱ፡፡ መሸጥንም ተዉ፡፡ ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነወ፡፡

:10

ሶለቲቱም በተፈጸመች ጊዜ በምድር ላይ ተበተኑ፡፡ ከአላህም ችሮታ ፈልጉ፡፡ አላህንም በብዙ አውሱ፡፡ ልትድኑ ይከጀላልና፡፡

:11

ንግድን ወይም ዛዛታን ባዩ ጊዜም ቆመህ የተዉህ ሲኾኑ ወደእርሷ ይበተናሉ፡፡ አላህ ዘንድ ያለው ዋጋ ከዛዛታም ከንግድም በላጭ ነው፡፡ «አላህም ከሰጪዎቹ ሁሉ ይበልጥ ሲሳይን ሰጭ ነው» በላቸው፡፡