ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

43 - The Ornaments of Gold - Az-Zukhruf

:1

ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡

:2

ገላጭ በኾነው መጽሐፍ እምላለሁ፡፡

:3

እኛ ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን አደረግነው፡፡

:4

እርሱም በመጽሐፎቹ እናት ውስጥ እኛ ዘንድ በእርግጥ ከፍተኛ ጥበብ የተመላ ነው፡፡

:5

ድንበር አላፊዎች ሕዝቦች ለመኾናችሁ ቁርኣኑን ከእናንተ ማገድን እናግዳለን?

:6

በፊተኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ከነቢይ ብዙን ልከናል፡፡

:7

ከነቢይም አንድም የሚመጣላቸው አልነበረም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩ ቢኾኑ እንጅ፡፡

:8

ከእነርሱም በኀይል ይበልጥ የበረቱትን አጥፍተናል፡፡ የፊተኞቹም (አጠፋፍ) ምሳሌ አልፏል፡፡

:9

«ሰማያትንና ምድርንም ማን ፈጠራቸው» ብለህ ብትጠይቃቸው «አሸናፊው ዐዋቂው (አላህ) በእርግጥ ፈጠራቸው» ይላሉ፡፡

:10

(እርሱ) ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ በርሷም ውስጥ ትምመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው፡፡

:11

ያም ከሰማያ ውሃን በልክ ያወረደላችሁ ነው፡፡ በእርሱም የሞተችውን አገር ሕያው አደረግን፡፡ እንደዚሁ (ከመቃብራችሁ) ትውወጣላችሁ፡፡

:12

ያም ዓይነቶችን ሁሉ የፈጠረ ለእናንተም ከመርከቦችና ከቤት እንስሳዎች የምትጋልቧቸውን ያደረገላችሁ ነው፡፡

:13

በጀርባዎቹ ላይ እንድትደላደሉ ከዚያም በርሱ ላይ የተደላደላችሁ ጊዜ የጌታችሁን ጸጋ እንድታስታውሱ፤ እንድትሉም፡- «ያ ይህንን የማንችለው ስንኾን ለእኛ ያገራለን ጌታ ጥራት ይገባው፡፡

:14

እኛም በእርግጥ ወደ ጌታችን ተመላሾች፤ነን» (እንድትሉ)፡፡

:15

ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን (ልጅን) አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡

:16

ከሚፈጥረው ውስጥ ሴቶች ልጆችን ያዘን? በወንዶች ልጆችም (እናንተን) መረጣችሁን?

:17

አንዳቸውም ለአልረሕማን ምሳሌ ባደረገው ነገር (በሴት ልጅ) በተበሰረ ጊዜ እርሱ በቁጭት የተመላ ኾኖ ፊቱ የጠቆረ ይኾናል፡፡

:18

በጌጥ (ተከልሶ) እንዲያድግ የሚደረገውን? እርሱም (ለደካማነቱ) በክርክር የሚያብራራውን ፍጡር (ሴትን) ለአላህ ያደርጋሉን?

:19

መላእክትንም እነርሱ የአልረሕማን ባሮች የኾኑትን ሴቶች አደረጉ፡፡ ሲፈጠሩ ነበሩን? መመስከራቸው በእርግጥ ትጻፋለች፡፡ ይጠየቃሉም፡፡

:20

«አልረሕማንም በሻ ኖሮ ባልተገዛናቸው ነበር» አሉ፡፡ ለእነርሱ በዚህ ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚዋሹ እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡

:21

ከእርሱ (ከቁርኣን) በፊት መጽሐፍን ሰጠናቸውን? ስለዚህ እነርሱ እርሱን የጨበጡ ናቸውን?

:22

ከቶውንም «እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘናቸው፡፡ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተመሪዎች ነን» አሉ፡፡

:23

(ነገሩ) እንደዚሁም ነው፡፡ ከበፊትህ በማንኛይቱም ከተማ ውስጥ አስፈራሪን አልላክንም፤ ቅምጥሎችዋ እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት ላይ አገኘን፤ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተከታዮች ነን ያሉ ቢኾኑ እንጅ፡፡

:24

(አስፈራሪው) «አባቶቻችሁን በእርሱ ላይ ከአገኛችሁበት ይበልጥ ቀጥተኛን (ሃይማኖት) ባመጣላችሁም?» አላቸው፡፡ «እኛ በእርሱ በተላካችሁበት ነገር ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡

:25

ከእነርሱም ተበቀልን፡፡ ያስተባባዮቹም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት፡፡

:26

ኢብራሂምም ለአባቱና ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኔ ከምትግገዙት ሁሉ ንጹሕ ነኝ፡፡»

:27

«ከዚያ ከፈጠረኝ በስተቀር (አልግገዛም)፡፡ እርሱ በእርግጥ ይመራኛልና፡፡»

:28

በዝርዮቹም ውስጥ ይመለሱ ዘንድ (ባንድ አምላክ ማመንን) ቀሪ ቃል አደረጋት፡፡

:29

ይልቅ እነዚህን (ቁረይሾችን)፣ አባቶቻቸውንም ቁርኣንና ገላጭ መልክተኛ እስከመጣላቸው ድረስ አጣቀምኳቸው፡፡

:30

እውነቱም በመጣላቸው ጊዜ «ይህ ድግምት ነው፡፡ እኛም በእርሱ ከሓዲዎች ነን» አሉ፡፡

:31

«ይህም ቁርኣን ከሁለቱ ከተሞች በታላቅ ሰው ላይ አይወረድም ኖሯልን?» አሉ፡፡

:32

እነርሱ የጌታህን ችሮታ ያከፈፍላሉን? እኛ በቅርቢቱ ሕይወት ኑሯቸውን በመካከላቸው አከፋፍለናል፡፡ ከፊላቸውም ከፊሉን ሠራተኛ አድርጎ ይይዝ ዘንድ ከፊላቸውን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች (በሀብት) አበለጥን፡፡ የጌታህም ጸጋ (ገነት) ከሚሰበስቡት (ሃብት) በላጨ ናት፡፡

:33

ሰዎችም (በክሕደት) አንድ ሕዝብ የሚኾኑ ባልነበሩ ኖሮ በአልረሕማን ፤ለሚክዱት ሰዎች (በዚህች ዓለም) ለቤቶቻቸው ከብር የኾኑን ጣራዎች በእነርሱ ላይ የሚወጡባቸውንም (የብር) መሰላሎች ባደረግንላቸው ነበር፡፡

:34

ለቤቶቻቸውም ደጃፎችን በእነርሱ ላይ የሚደገፉባቸውንም አልጋዎች (ከብር ባደረግንላቸው ነበር)፡፡

:35

የወርቅ ጌጥንም (ባደረግንላቸው ነበር)፡፡ ይህም ሁሉ የቅርቢቱ ሕይወት መጣቀሚያ እንጅ ሌላ አይደለም፤ (ጠፊ ነው)፡፡ መጨረሻይቱም አገር በጌታህ ዘንድ ለጥንቁቆቹ ናት፡፡

:36

ከአልረሕማን ግሣጼ (ከቁርኣን) የሚደናበርም ሰው ለእርሱ ሰይጣንን እናስጠጋለን፡፡ ስለዚህ እርሱ ለእርሱ ቁራኛ ነው፡፡

:37

እነርሱም (ተደናባሪዎቹ) ተመሪዎች መኾናቸውን የሚያስቡ ሲኾኑ እነርሱ (ሰይጣናት) ከቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ያግዷቸዋል፡፡

:38

(በትንሣኤ) ወደኛ በመጣም ጊዜ (ቁራኛዬ ሆይ!) «በእኔና ባንተ መካከል የምሥራቅና የምዕራብ ርቀት በኖረ ወይ ምኞቴ! ምን የከፋህ ቁራኛ ነህ» ይላል፡፡

:39

ስለ በደላችሁም ዛሬ እናንተ በቅጣት ተጋሪዎች መኾናችሁ አይጠቅማችሁም፤ (ይባላሉ)፡፡

:40

አንተ ደንቆሮዎችን ታሰማለህን? ወይስ ዕውሮችንና በግልጽ ጥመት ውስጥ የኾኑን ሰዎች ትመራለህን?

:41

አንተንም (ቅጣታቸውን ስታይ) ብንወስድህ እኛ ከእነርሱ ተበቃዮች ነን፡፡

:42

ወይም ያንን የቀጠርናቸውን ብናሳይህ እኛ በእነርሱ (ቅጣት) ላይ ቻይዎች ነን፡፡

:43

ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና፡፡

:44

እርሱም (ቁርኣን) ለአንተ፣ ለሕዘቦችህም ታላቅ ክብር ነው፡፡ ወደ ፊትም (ከርሱ) ትጠየቃላችሁ፡፡

:45

ከመልእክተኞቻችንም ካንተ በፊት የላክናቸውን (ተከታዮቻቸውን) ከአልረሕማን ሌላ የሚገዙዋቸው የኾኑን አማልክት አድርገን እንደ ኾነ ጠይቃቸው፡፡

:46

ሙሳንም በተዓምራቶቻችን ወደ ፈርዖንና ወደ ሹማምንቶቹ በእርግጥ ላክን፡፡ «እኔ የዓለማት ጌታ መልክተኛ ነኝ» አላቸውም፡፡

:47

በተዓምራታችንም በመጣባቸው ጊዜ ወዲያውኑ እነርሱ በእርሷ ይስቃሉ፡፡

:48

ከተዓምርም አንዲትንም አናሳያቸውም እርሷ ከብጤዋ በጣም የበለጠች ብትኾን እንጅ፡፡ (ከክህደታቸው) ይመለሱም ዘንድ በቅጣት ያዝናቸው፡፡

:49

«አንተ ድግምተኛ (ዐዋቂ) ሆይ! ጌታህን አንተ ዘንድ ቃል በገባልህ ለእኛ ለምንልን፡፡ እኛ (ቅጣቱን ቢያነሳልን) ተመሪዎች ነን» አሉም፡፡

:50

ስቃዩን ከእነርሱ ላይ በገለጥንም ጊዜ ወዲያውኑ ኪዳናቸውን ያፈርሳሉ፡፡

:51

ፈርዖንም በሕዝቦቹ ውስጥ ተጣራ፡፡ አለም፤ «ሕዝቦቼ ሆይ! የምስር ግዛት የኔ አይደለምን? እነዚህም ጅረቶች ከስሬ የሚፈሱ ሲኾኑ (የኔ አይደሉምን?) አትመለከቱምን?

:52

«በውነቱ እኔ ከዚህ ያ እርሱ ወራዳ ንግግሩንም ሊገልጽ የማይቀርብ ከኾነው በላጭ ነኝ፡፡

:53

«በእርሱም ላይ የወርቅ አንባሮች ለምን አልተጣሉበትም ወይም መላእክት ከእርሱ ጋር ተቆራኝተው ለምን አልመጡም» (አለ)፡፡

:54

ሕዝቦቹንም አቄላቸው፡፡ ታዘዙትም፡፡ እነርሱ አመጸኞች ሕዝቦች ነበሩና፡፡

:55

ባስቆጡንም ጊዜ ከእነርሱ በተበቀለን፡፡ ሁሉንም አሰጠምናቸውም፡፡

:56

(በጥፋት) ቀዳሚዎችና ለኋለኞቹ (መቀጣጫ) ምሳሌም አደረግናቸው፡፡

:57

የመርየም ልጅም ምሳሌ በተደረገ ጊዜ ሕዝቦችህ (ከሓዲዎቹ) ወዲያውኑ ከእርሱ ይስቃሉ፡፡

:58

«አማልክቶቻችን ይበልጣሉን ወይስ እርሱ?» አሉም፡፡ ለክርክርም እንጅ ላንተ እርሱን ምሳሌ አላደረጉትም፡፡ በእውነት እነርሱ ክርክረ ብርቱ ሕዝቦች ናቸው፡፡

:59

እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡

:60

ብንሻም ኖሮ በምድር ላይ ከእናነተ ምትክ መላእክትን ባደረግን ነበር፡፡

:61

እርሱም (ዒሳ) ለሰዓቲቱ (ማወቂያ) በእርግጥ ምልክት ነው፡፡ «በእርሷም አትጠራጠሩ፡፡ ተከተሉኝም፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» (በላቸው)፡፡

:62

ሰይጣንም አያግዳችሁ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡

:63

ዒሳ በታምራቶች በመጣ ጊዜም አላቸው «በእርግጥ በጥበብ መጣኋችሁ፡፡ የዚያንም በርሱ የምትለያዩበትን ከፊሉን ለናንተ ላብራራላችሁ (መጣሁ)፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ታዘዙኝም፡፡

:64

«አላህ ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት፡፡ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»

:65

ከመካከላቸውም አሕዛቦቹ ተለያዩ፡፡ ለእነዚያም ለበደሉት ከአሳማሚ ቀን ቅጣት ወዮላቸው፡፡

:66

ሰዓቲቱን እነርሱ የማያውቁ ኾነው በድንገት ልትመጣባቸው እንጅ ይጠባበቃሉን?

:67

ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው፡፡ አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ፡፡

:68

(ለነርሱስ) «ባሮቼ ሆይ! ዛሬ ቀን በእናንተ ላይ ፍርሃት የለባችሁም እናንተም የምታዝኑ አይደላችሁም» (ይባላሉ)፡፡

:69

እነዚያ በአንቀጾቻችን ያመኑና ፍጹም ታዛዦች የነበሩ (ባሮቼ ሆይ!)

:70

«ገነትን ግቡ እናንተም ሚስቶቻችሁም ትደሰታላችሁ ትከበሩም አላችሁ» (ይባላሉ)፡፡

:71

ከወርቅ የኾኑ ሰፋፊ ዝርግ ሳሕኖችና ኩባያዎች በእነርሱ ላይ ይዝዞራሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ነፍሶች የሚከጅሉት፣ ዓይኖችም የሚደሰቱበት ሁሉ አልለ፡፡ እናንተም በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ናችሁ፡፡

:72

ይህችም ያቺ ትሠሩት በነበራችሁት ዋጋ የተሰጣችኋት ገነት ናት፡፡

:73

ለእናንተ በውስጧ ብዙ ፍረፍሬዎች በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡

:74

አመጸኞች በገሀነም ስቃይ ውስጥ በእርግጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡

:75

ከእነርሱ (ቅጣቱ) አይቀለልላቸውም፡፡ እነርሱም በእርሱ ውስጥ ተሰፋ ቆራጮች ናቸው፡፡

:76

አልበደልናቸውምም፤ ግን በዳዮቹ እነርሱው ነበሩ፡፡

:77

«ማሊክ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ (በሞት) ይፍረድ፡፡» እያሉ ይጣራሉም፡፡ «እናንተ (በቅጣቱ ውስጥ) ዘላለም ነዋሪዎች ናችሁ» ይላቸዋል፡፡

:78

እውነተኛውን መንገድ በእርግጥ አመጣንላችሁ፡፡ ግን አብዛኞቻችሁ እውነቱን ጠይዎች ናችሁ፡፡

:79

ይልቁንም (በነቢዩ ላይ በማደም) ነገርን አጠነከሩን? እኛም (ተንኮላቸውን ወደእነርሱ በመመለስ) አጠንካሪዎች ነን፡፡

:80

ወይም እኛ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የማንሰማ መኾናችንን ያስባሉን? አይደለም፤ መልክተኞቻችንም እነርሱ ዘንድ ይጽፋሉ፡፡

:81

«ለአልረሕማን ልጅ (የለውም እንጅ) ቢኖረው እኔ (ለልጁ) የተገዢዎቹ መጀመሪያ ነኝ» በላቸው፡፡

:82

የሰማያትና የምድር ጌታ የዙፋኑ ጌታ ከሚሉት ነገር ሁሉ ጠራ፡፡

:83

ተዋቸውም፡፡ ያንን ይስፈራሩበት የነበሩትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ (በስሕተታቸው ውስጥ) ይዋኙ ይጫዎቱም፡፡

:84

እርሱም ያ በሰማይ ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው በምድርም ውስጥ ሊግገዙት የሚገባው አምላክ ነው፡፡ እርሱም ብልሃተኛው ዐዋቂው ነው፡፡

:85

ያም የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የእርሱ ብቻ የኾነው አምላክ ላቀ፡፡ የሰዓቲቱም (የመምጫዋ ዘመን) ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡

:86

እነዚያም ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸው እነርሱ የሚያውቁ ኾነው በእውነት ከመሰከሩት በስተቀር ምልጃን አይችሉም፡፡

:87

ማን እንደፈጠራቸውም ብትጠይቃቸው «በእርግጥ አላህ ነው» ይላሉ፡፡ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ይዞራሉ፡፡

:88

(ነቢዩ) ጌታዬ ሆይ! እነዚህ የማያምኑ ሕዝቦች ናቸው፤ የማለቱም (ዕውቀት አላህ ዘንድ ነው)፡፡

:89

እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ነገሬ ሰላም ነው በልም፡፡ ወደፊትም (የሚመጣባቸውን) ያውቃሉ፡፡