ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

37 - Those who set the Ranks - Aş-Şāffāt

:1

መሰለፍን በሚሰለፉት፡፡

:2

መገሠጽንም በሚገሥጹት፤

:3

ቁርኣንንም በሚያነቡት እምላለሁ፡፡

:4

አምላካችሁ በእርግጥ አንድ ነው፡፡

:5

የሰማያትና የምድር በመካከላቸው ያለውም ፍጡር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምሥራቆችም ጌታ ነው፡፡

:6

እኛ ቅርቢቱን ሰማይ በከዋክብት ጌጥ አጌጥናት፡፡

:7

አመጸኛም ከሆነ ሰይጣን ሁሉ መጠበቅን ጠበቅናት፡፡

:8

ወደላይኛው ሰራዊት አያዳምጡም፡፡ ከየወገኑም ሁሉ ችቦ ይጣልባቸዋል፡፡

:9

የሚባረሩ ሲሆኑ (ይጣልባቸዋል)፡፡ ለእነሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡

:10

ንጥቂያን የነጠቀ ወዲያውም አብሪ ኮከብ የተከተለው ሲቀር፤ (እርሱ ይሰማዋል)፡፡

:11

ጠይቃቸውም፤ እነርሱ በአፈጣጠር ይበልጥ የበረቱ ናቸውን? ወይስ እኛ (ከእነርሱ በፊት) የፈጠርነው? (ፍጡር) እኛ ከሚጣበቅ ጭቃ ፈጠርናቸው፡፡

:12

ይልቁንም (በማስተባበላቸው) ተደነቅህ፤(ከመደነቅህ) ይሳለቃሉም፡፡

:13

በተገሠጹም ጊዜ አይመለሱም፡፡

:14

ተዓምርን ባዩም ጊዜ ለመሳለቅ ይጠራራሉ፡፡

:15

ይላሉም «ይህ ግልጽ ድግምት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

:16

«በሞትንና ዐፈርና አጥንቶችም በኾን ጊዜ እኛ የምንቀሰቀስ ነን?

:17

«የቀድሞዎቹ አባቶችንም? (ይላሉ)፡፡

:18

«አዎን እናንተ ወራዶች ሆናችሁ (ትነሳላችሁ)» በላቸው፡፡

:19

እርሷም አንዲት ጩኸት ብቻ ናት፡፡ እነርሱም ወዲያውኑ (ምን እንደሚፈጸምባቸው) ያያሉ፡፡

:20

«ዋ ጥፋታችን! ይህ የፍርዱ ቀን ነው» ይላሉም፡፡

:21

«ይህ ያ በእርሱ ታስተባብሉ የነበራችሁት መለያው ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡

:22

(ለመላእክቶችም) «እነዚያን ነፍሶቻቸውን የበደሉትን ሰዎች ጓደኞቻቸውንም ይግገዟቸው የነበሩትንም (ጣዖታት) ሰብስቡ፡፡

:23

«ከአላህ ሌላ (የሚገዙዋቸውን ሰብስቧቸው) ወደ እሳት መንገድም ምሩዋቸው፡፡

:24

«አቁሟቸውም፡፡ እነርሱ ተጠያቂዎች ናቸውና» (ይባላል)፡፡

:25

(ለእነርሱም) «የማትረዳዱት ለእናንተ ምን አላችሁ? (ይባላሉ)፡፡

:26

በእርግጥ እነርሱ ዛሬ እጃቸውን የሰጡ ወራዳዎች ናቸው፡፡

:27

የሚወቃቀሱም ሆነው ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ይመጣሉ፡፡

:28

(ለአስከታዮቹ) እናንተ ከስተቀኝ ትመጡብን ነበር ይላሉ፡፡

:29

(አስከታዮቹም) ይላሉ «አይደለም ፈጽሞ ምእምናን አልነበራችሁም፡፡

:30

«ለእኛም በእናንተ ላይ ምንም ስልጣን አልነበረንም፡፡ በእርግጥ እናንተ ጠማሞች ሕዝቦች ነበራችሁ፡፡

:31

«በእኛም ላይ የጌታችን ቃል ተረጋገጠብን፤ እኛ (ሁላችንም ቅጣቱን) ቀማሾች ነን፡፡

:32

«ወደ ጥምመት ጠራናችሁም፡፡ እኛ ጠማሞች ነበርንና» (ይላሉ)፡፡

:33

ስለዚህ እነርሱ በዚያ ቀን በቅጣቱ ነጋሪዎች ናቸው፡፡

:34

እኛ በአመጸኞች ሁሉ እንደዚሁ እንሠራለን፡፡

:35

እነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበሩ፡፡

:36

እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተው ነን? ይሉም ነበር፡፡

:37

አይደለም እውነቱን (ሃይማኖት) አመጣ፡፡ መልክተኞቹንም እውነተኛነታቸውን አረጋገጠ፡፡

:38

እናንተ አሳማሚውን ቅጣት በእርግጥ ቀማሾች ናችሁ፡፡

:39

ትሠሩትም የነበራችሁትን እንጂ ሌላን አትመነዱም፡፡

:40

ግን ምርጥ የሆኑት የአላህ ባሮች (ቅጣትን አይቀምሱም)፡፡

:41

እነዚያ ለእነርሱ የታወቀ ሲሳይ አላቸው፡፡

:42

ፍራፍሬዎች (አሏቸው) እነርሱም የተከበሩ ናቸው፤

:43

በድሎት ገነቶች ውስጥ፡፡

:44

ፊት ለፊት የሚታያዩ ሲሆኑ በአልጋዎች ላይ (ይንፈላሰሳሉ)፡፡

:45

ከሚመነጭ ወይን ጠጅ በያዘ ብርጭቆ በእነርሱ ላይ ይዞርባቸዋል፡፡

:46

ነጭ ለጠጪዎች ጣፋጭ ከኾነች፡፡

:47

በእርሷ ውስጥም ምታት የለባትም፡፡ እነርሱም ከእርሷ የሚሰክሩ አይደሉም፡፡

:48

እነርሱም ዘንድ ዓይናቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች የኾኑ ዓይናማዎች አልሉ፡፡

:49

እነርሱ ልክ የተሸፈነ (የሰጎን) ዕንቁላል ይመስላሉ፡፡

:50

የሚጠያየቁም ሆነው ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ይመጣሉ፡፡

:51

ከእነርሱ የሆነ ተናጋሪ ይላል «እኔ ጓደኛ ነበረኝ፡፡

:52

«በእርግጥ አንተ ከሚያምኑት ነህን? የሚል፡፡

:53

«በሞትንና ዐፈር አጥንቶችም በሆን ጊዜ እኛ በእርግጥ እንመረመራለን?» (የሚል)፡፡

:54

እናንተ ተመልካቾች ናችሁን? ይላል፡፡

:55

ይመለከታልም፤ በገሀነም መካከልም (ጓደኛውን) ያየዋል፡፡

:56

ይላል «በአላህ እምላለሁ፤ በእርግጥ ልታጠፋኝ ቀርበህ ነበር፡፡

:57

«የጌታየም ጸጋ ባልነበረ ኖሮ ወደ እሳት ከሚቀርቡት እሆን ነበር፡፡»

:58

(የገነት ሰዎች ይላሉ) «እኛ የምንሞት አይደለንምን?

:59

«የመጀመሪያይቱ መሞታችን ብቻ ስትቀር፡፡ እኛም የምንቅቀጣ አይደለንምን?» (ይላሉ)፡፡

:60

ይህ (ለገነት ሰዎች የተወሳው) እርሱ በእርግጥ ታላቅ ዕድል ነው፡፡

:61

ለዚህ ብጤ ሠሪዎች ይሥሩ፡፡

:62

በመስተንግዶነት ይህ ይበልጣልን? ወይስ የዘቁም ዛፍ?

:63

እኛ ለበዳዮች ፈተና አድርገናታል፡፡

:64

እርሷ በገሀነም አዘቅት ውስጥ የምትወጣ ዛፍ ናት፡፡

:65

እንቡጧ ልክ የሰይጣናት ራሶች ይመስላል፡፡

:66

እነርሱም ከእርሷ በይዎች ናቸው፤ ሆዶችንም ከእርሷ ሞይዎች ናቸው፡፡

:67

ከዚያም ለእነርሱ በእርሷ ላይ ከተኳሳ ውሃ ቅልቅል (መጠጥ) አልላቸው፡፡

:68

ከዚያም መመለሻቸው ወደ ተጋጋመች እሳት ነው፡፡

:69

እነሱ አባቶቻቸውን የተሳሳቱ ሆነው አግኝተዋልና፡፡

:70

እነሱም በፈለጎቻቸው ላይ ይገሰግሳሉና፡፡

:71

ከእነርሱ በፊትም የቀድሞዎቹ (ሕዝቦች) አብዛኞቻቸው በእርግጥ ተሳስተዋል፡፡

:72

በውስጣቸውም አስፈራሪዎችን በእርግጥ ልከናል፡፡

:73

የተስፈራሪዎቹም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከት፡፡

:74

ምርጥ የሆኑት የአላህ ባሮች ብቻ ሲቀሩ፡፡

:75

ኑሕም በእርግጥ ጠራን፡፡ ጥሪውን ተቀባዮቹም ምንኛ አማርን!

:76

እርሱንም ቤተሰቦቹንም ከከባድ ጭንቅ አዳንን፡፡

:77

ዘሮቹንም እነርሱን ብቻ ቀሪዎች አደረግን፤

:78

በርሱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ (መልካም ዝናን) ተውን፡፡

:79

«በዓለማት ውስጥ ሰላም በኑሕ ላይ ይኹን፡፡»

:80

እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

:81

እርሱ ከምእምናን ባሮቻችን ነውና፡፡

:82

ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡

:83

ኢብራሂምም በእርግጥ ከተከታዮቹ ነው፡፡

:84

ወደ ጌታው በቅን ልብ በመጣ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡፡

:85

«ለአባቱና ለሕዝቦቹ ምንን ትግገዛላችሁ?» ባለ ጊዜ፡፡

:86

«ለቅጥፈት ብላችሁ ከአላህ ሌላ አማልክትን ትሻላችሁን?

:87

«በዓለማትም ጌታ ሃሳባችሁ ምንድን ነው?» አለ፡፡

:88

በከዋክብትም መመልከትን ተመለከተ፡፡

:89

«እኔ በሽተኛ ነኝም» አለ፡፡

:90

ከእርሱም የሸሹ ሆነው ኼዱ፡፡

:91

ወደ አማልክቶቻቸውም ተዘነበለ፡፡ አለም፡- «አትበሉምን?»

:92

«የማትናገሩት ለናንተ ምን አላችሁ?»

:93

በኀይል የሚመታቸውም ሆኖ በእነርሱ ላይ በድብቅ ተዘነበለ፡፡

:94

ወደእርሱም (ሰዎቹ) እየሮጡ መጡ፡፡

:95

አላቸው «የምትጠርቡትን ትግገዛላችሁን?»

:96

«አላህ እናንተንም የምትሠሩትንም የፈጠረ ሲኾን፡፡»

:97

«ለእርሱም ግንብን ገንቡ በእሳት ነበልባል ውስጥ ጣሉትም» አሉ፡፡

:98

በእርሱም ተንኮልን አሰቡ፡፡ ዝቅተኞችም አደረግናቸው፡፡

:99

አለም «እኔ ወደ ጌታዬ ኼያጅ ነኝ፡፡ በእርግጥ ይመራኛልና፡፡»

:100

ጌታዬ ሆይ! ከመልካሞቹ የሆነን (ልጅ) ስጠኝ፡፡

:101

ታጋሽ በሆነ ወጣት ልጅም አበሰርነው፡፡

:102

ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡

:103

ሁለቱም ትዕዛዙን በተቀበሉና በግንባሩም ጎን ላይ በጣለው ጊዜ (የሆነው ሆነ)፡፡

:104

ጠራነውም፤ (አልነው) «ኢብራሂም ሆይ!

:105

ራእይቱን በእውነት አረጋገጥክ፡፡» እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

:106

ይህ እርሱ በእውነት ግልጽ ፈተና ነው፡፡

:107

በታላቅ ዕርድም (መስዋዕት) ተቤዠነው፡፡

:108

በእርሱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን አስቀረንለት፡፡

:109

ሰላም በኢብራሂም ላይ ይሁን፡፡

:110

እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡

:111

እርሱ በእርግጥ ካመኑት ባሮቻችን ነው፡፡

:112

በኢስሐቅም አበሰርነው፡፡ ከመልካሞቹ የሆነ ነቢይ ሲሆን፡፡

:113

በእርሱና በኢስሐቅ ላይም ባረክን፡፡ ከሁለቱም ዘሮች በጎ ሠሪ አልለ፡፡ ለነፍሱ ግልጽ በዳይም አለ፡፡

:114

በሙሳና በሃሩን ላይም በእርግጥ ለገስን፡፡

:115

እነርሱንም ሕዝቦቻቸውንም ከታላቅ ጭንቅ አዳንን፡፡

:116

ረዳናቸውም፡፡ እነርሱም አሸናፊዎች ነበሩ፡፡

:117

በጣም የተብራራውንም መጽሐፍ ሰጠናቸው፡፡

:118

ቀጥተኛውንም መንገድ መራናቸው፡፡

:119

በሁለቱም ላይ በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን ተውንላቸው፡፡

:120

ሰላም በሙሳና በሃሩን ላይ ይሁን፡፡

:121

እኛ እንደዚሁ በጎ አድራጊዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡

:122

ሁለቱም በእርግጥ ከአመኑት ባሮቻችን ናቸው፡፡

:123

ኢልያስም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

:124

ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ አላህን አትፈሩምን?

:125

በዕልን ትገዛላችሁን? ከሰዓሊዎቹ ሁሉ ይበልጥ በጣም አሳማሪ የሆነውንም አምላክ ትተዋላችሁን?

:126

አላህን ጌታችሁንና የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁን ጌታ (ትተዋላችሁን)?

:127

አስተባበሉትም፡፡ ስለዚህ እነርሱ (ለቅጣት) የሚጣዱ ናቸው፡፡

:128

ንጹሕ የተደረጉት የአላህ ባሮች ብቻ ሲቀሩ፡፡

:129

በእርሱ ላይም በኋለኞቹ ሕዝቦች ውስጥ መልካም ዝናን ተውንለት፡፡

:130

ሰላም በኢልያሲን ላይ ይሁን፡፡

:131

እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን፡፡

:132

እርሱ በእርግጥ ከምእመናን ባሮቻችን ነው፡፡

:133

ሉጥም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

:134

እርሱንና ቤተሰቦቹን ሁሉንም በአዳንናቸው ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:135

(በቅጣቱ ውስጥ) ከቀሪዎቹ የሆነችው አሮጊት ብቻ ስትቀር፡፡

:136

ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡

:137

እናንተም ያነጋችሁ ስትሆኑ በእነርሱ (መኖሪያዎች) ላይ (በቀን) ታልፋላችሁ፡፡

:138

በሌሊትም (ታልፋላችሁ)፤ ልብም አታደርጉምን?

:139

ዩኑስም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡

:140

ወደ ተመላው መርከብ በኮበለለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:141

ዕጣም ተጣጣለ፡፡ ከተሸነፉትም ሆነ፡፡

:142

እርሱም ተወቃሽ ሲሆን ዐሳው ዋጠው፡፡

:143

እርሱ ለጌታው ከአወዳሾቹ ባልሆነም ኖሮ፤

:144

እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ በሆዱ ውስጥ በቆየ ነበር፡፡

:145

እርሱ በሽተኛ ሆኖ በቃይ በሌለው (በባሕር) ዳርቻ ላይ ጣልነውም፡፡

:146

በእርሱም ላይ (በአጠገቡ) ከቅል የሆነችን ዛፍ አበቀልን፡፡

:147

ወደ መቶ ሺሕ ሰዎችም (ዳግመኛ) ላክነው፡፡ ከቶውንም ይጨምራሉ፡፡

:148

አመኑም፡፡ እስከ ጊዜ ድረስም አጣቀምናቸው፡፡

:149

(የመካን ሰዎች) ጠይቃቸውም፡፡ «ለጌታህ ሴቶች ልጆች ለእነርሱም ወንዶች ልጆች ይኖራልን?»

:150

ወይስ እኛ እነርሱ የተጣዱ ሆነው መላእክትን ሴቶች አድርገን ፈጠርን?

:151

ንቁ! እነርሱ ከቅጥፈታቸው (የተነሳ) ይላሉ፡-

:152

«አላህ (መላእክትን) ወለደ፡፡» እነርሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፡፡

:153

በወንዶች ልጆች ላይ ይልቅ ሴቶችን ልጆች መረጥን?

:154

ለእናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ!

:155

አትገነዘቡምን?

:156

ወይስ ለእናንተ ግልጽ አስረጅ አላችሁን?

:157

«እውነተኞች እንደ ሆናችሁ መጽሐፋችሁን አምጡ» (በላቸው)፡፡

:158

በአላህና በአጋንንት መካከልም ዝምድናን አደረጉ፡፡ አጋንንትም እነርሱ (ይህን ባዮች በእሳት) የሚጣዱ መሆናቸውን በእርግጥ ዐውቀዋል፡፡

:159

አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ፡፡

:160

ግን የተመረጡት የአላህ ባሮች (በአላህ ላይ አይዋሹም)፡፡

:161

እናንተም የምትገዟቸውም ሁሉ፤

:162

በእርሱ (በአላህ) ላይ አንድንም አጥማሚዎች አይደላችሁም፡፡

:163

ያንን እርሱ ገሀነምን ገቢ የሆነውን ሰው ቢሆን እንጅ፡፡

:164

(ጂብሪል አለ) ከእኛም አንድም የለም፤ ለእርሱ የታወቀ ደረጃ ያለው ቢሆን እንጅ፡፡

:165

እኛም (ጌታን ለመግገዛት) ተሰላፊዎቹ እኛ ነን፡፡

:166

እኛም (አላህን) አጥሪዎቹ እኛ ነን፡፡

:167

እነርሱም (ከሓዲዎቹ) በእርግጥ ይሉ ነበሩ፡-

:168

«ከቀድሞዎቹ (መጻሕፍት) ገሳጭ መጽሐፍ እኛ ዘንድ በነበረን ኖሮ፤

:169

«የአላህ ምርጦች ባሮች በሆን ነበር፡፡»

:170

ግን (ቁርኣኑ በመጣላቸው ጊዜ) በእርሱ ካዱ፡፡ ወደፊትም በእርግጥ ያውቃሉ፡፡

:171

(የእርዳታ) ቃላችንም መልክተኞች ለሆኑት ባሮቻችን በእውነት አልፋለች፡፡

:172

እነርሱ ተረጂዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡

:173

ሰራዊቶቻችንም በእርግጥ አሸናፊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡

:174

ከእነርሱም (ከመካ ከሓዲዎች) እስከ ጥቂት ጊዜ ድረስ ዙር (ተዋቸው)፡፡

:175

እያቸውም ወደፊትም (የሚደርስባቸውን) ያያሉ፡፡

:176

በቅጣታችንም ያቻኩላሉን?

:177

በቀያቸውም በወረደ ጊዜ የተስፈራሪዎቹ ንጋት ከፋ!

:178

እነርሱንም እስከ (ጥቂት) ጊዜ ድረስ ተዋቸው፡፡

:179

ተመልከትም በእርግጥም ያያሉ፡፡

:180

የማሸነፍ ጌታ የሆነው ጌታህ ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡

:181

በመልክተኞቹም ላይ ሰላም ይኹኑ፤

:182

ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፡፡