ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

32 - The Prostration - As-Sajdah

:1

አ.ለ.መ (አሊፍ ላም ሚም)፡፡

:2

የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፡፡ ከዓለማት ጌታ ነው፡፡

:3

ይልቁንም «ቀጠፈው» ይላሉን? አይደለም፡፡ እርሱ ከጌታህ ዘንድ የሆነ እውነት ነው፡፡ በእርሱ ከአንተ በፊት ከአስፈራሪ (ነቢይ) ያልመጣባቸውን ሕዝቦች ልታስፈራራበት (ያወረደልህ ነው)፡፡ እነርሱ ሊምመሩ ይከጀላልና፡፡

:4

አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ለሱ ክብር በሚስማማ መልኩ) የተደላደለ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም፤ አትገሰጹምን?

:5

ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ከምትቆጥሩት (ዘመን) ልኩ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ወደርሱ ይወጣል (ይመለሳል)፡፡

:6

ይህ (ይህንን የሠራው) ሩቁንም ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂው አሸናፊው፣ አዛኙ (ጌታ) ነው፡፡

:7

ያ የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረው የሰውንም ፍጥረት ከጭቃ የጀመረው ነው፡፡

:8

ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ፣ ከደካማ ውሃ ያደረገ ነው፡፡

:9

ከዚያም (ቅርጹን) አስተካከለው፡፡ በእርሱ ውስጥም ከመንፈሱ ነፋበት፤ (ነፍስ ዘራበት)፡፡ ለእናንተም ጆሮዎችን፣ ዓይኖችንና ልቦችንም አደረገላችሁ፡፡ በጣም ጥቂትን ብቻ ታመሰግናላችሁ፡፡

:10

«በምድርም ውስጥ (በስብሰን) በጠፋን ጊዜ እኛ በአዲስ መፈጠር ውስጥ እንሆናለን?» አሉ፡፡ በእውነቱ እነርሱ በጌታቸው መገናኘት ከሓዲዎች ናቸው፡፡

:11

«በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡

:12

አመጸኞችም በጌታቸው ዘንድ ራሶቻቸውን ያቀረቀሩ ሆነው «ጌታችን ሆይ! አየን፣ ሰማንም፡፡ መልካምን እንሠራለንና (ወደ ምድረ ዓለም) መልሰን፡፡ እኛ አረጋጋጮች ነን፡፡» (የሚሉ ሲሆኑ) ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)፡፡

:13

በሻንም ኖሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷን) በሰጠናት ነበር፡፡ ግን ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች የተሰበሰቡ ሆነው በእርግጥ እሞላለሁ ማለት ቃሉ ከእኔ ተረጋግጧል፡፡

:14

ይህንንም ቀናችሁን መገናኘትን በመርሳታችሁ ምክንያት (ቅጣትን) ቅመሱ! እኛ ተውናችሁ፡፡ ትሠሩት በነበራችሁትም ጥፋት ዘውታሪን ቅጣት ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡

:15

በአንቀጾቻችን የሚያምኑት እነዚያ በእርሷ በተገሰጹ ጊዜ ሰጋጆች ሆነው የሚወድቁትና እነርሱም የማይኮሩ ሆነው በጌታቸው ምስጋና (ተጎናጽፈው) የሚያወድሱት ብቻ ናቸው፡፡

:16

ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ሆነው ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፡፡ ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ፡፡

:17

ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም፡፡

:18

አማኝ የሆነ ሰው አመጸኛ እንደ ሆነ ሰው ነውን? አይስተካከሉም፡፡

:19

እነዚያ ያመኑና መልካሞችን የሰሩማ ለእነርሱ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መስተንግዶ ሲሆኑ መኖሪያ ገነቶች አሏቸው፡፡

:20

እነዚያ ያመጹትማ፤ መኖሪያቸው እሳት ናት፡፡ ከእርሷ መውጣትን በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ለእነርሱም «ያንን በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» ይባላሉ፡፡

:21

ይመለሱ ዘንድም ከትልቁ ቅጣት በፊት (በዚህ ዓለም) ከትንሹ ቅጣት በእርግጥ እናቀምሳቸዋለን፡፡

:22

በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን፡፡

:23

ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እርሱን ከመገናኘትህም በመጠራጠር ውስጥ አትሁን፡፡ ለእስራኤል ልጆችም መሪ አደረግነው፡፡

:24

በታገሱና በተዓምራቶቻችን የሚያረጋግጡ በሆኑም ጊዜ ከእነርሱ በትዕዛዛችን የሚመሩ መሪዎች አደረግን፡፡

:25

ጌታህ እርሱ በዚያ በእርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው (በፍርድ) ይለያል፡፡

:26

ከክፍለ ዘመናት ሰዎች ብዙዎችን ያጠፋን መሆናችን በመኖሪያዎቻቸው የሚሄዱ ሲሆኑ

:27

እኛ ውሃን ወደ ደረቅ ምድር የምንነዳ እንስሶቻቸውና ነፍሶቻቸው ከእርሱ የሚበሉለትንም አዝመራ በእርሱ የምናወጣ መኾናችንን አያዩምን? አይመለከቱምን?

:28

«ከእውነተኞችም እንደሆናችሁ ይህ ፍርድ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡

:29

«በፍርድ ቀን እነዚያን የካዱትን ሰዎች እምነታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ እነርሱም ጊዜን አይሰጡም፤» በላቸው፡፡

:30

እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ተጠባበቅም፤ እነርሱ ተጠባባቂዎች ናቸውና፡፡