ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

26 - The Poets - Ash-Shu`arā

:1

ጠ.ሰ.መ. (ጧ ሲን ሚም)፡፡

:2

ይህች ግልጽ ከኾነው መጽሐፍ አንቀጾች ናት፡፡

:3

አማኞች ባለመኾናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መኾን ይፈራልሃል፡፡

:4

ብንሻ በእነሱ ላይ ከሰማይ ተዓምረን እናወርድና አንገቶቻቸው (መሪዎቻቸው) ለእርሷ ተዋራጆች ይኾናሉ፡፡

:5

ከአልረሕማንም ዘንድ ኣዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፤ ከእርሱ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጂ፡፡

:6

በእርግጥም አስተባበሉ፡፡ የዚያም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ወሬዎች (ፍጻሜ) ይመጣባቸዋል፡፡

:7

ወደ ምድርም በውስጧ ከመልካም (በቃይ) ጎሳ ሁሉ ብዙን እንዳበቀልን አላዩምን፡፡

:8

በዚህ አስደናቂ ምልክት አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡

:9

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡

:10

ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:11

«ወደ ፈርዖን ሕዝቦች (ኺድ) አላህን አይፈሩምን» (አለው)፡፡

:12

(ሙሳም) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁ፡፡

:13

«ልቤም ይጠብባል፡፡ ምላሴም አይፈታም፡፡ ስለዚህ ወደ ሃሩን ላክ፡፡

:14

«ለእነርሱም በእኔ ላይ (የደም) ወንጀል አልለ፡፡ ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ፡፡»

:15

(አላህ) አለ «ተው! (አይነኩህም)፡፡ በተዓምራቶቻችንም ኺዱ፡፡ እኛ ከእናንተ ጋር ሰሚዎች ነንና፡፡

:16

«ወደ ፈርዖንም ኺዱ፡፡ በሉትም፡- እኛ የዓለማት ጌታ መልክተኞች ነን፡፡

:17

«የእስራኤልን ልጆች ከእኛ ጋር ልቀቅ፡፡»

:18

(ፈርዖንም) አለ «ልጅ ኾነህ በእኛ ውስጥ አላሳደግንህምን በእኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን

:19

«ያችንም የሠራሃትን ሥራህን አልሠራህምን አንተም ከውለታ ቢሶቹ ነህ» (አለ)፡፡

:20

(ሙሳም) አለ «ያን ጊዜ እኔም ከተሳሳቱት ኾኜ ሠራኋት፡፡

:21

«በፈራኋችሁም ጊዜ ከእንናተ ሸሸሁ፡፡ ጌታየም ለእኔ ጥበብን ሰጠኝ፡፡ ከመልክተኞቹም አደረገኝ፡፡

:22

«ይህችም የእስራኤልን ልጆች ባሪያ በማድረግህ በእኔ ላይ የምትመጻደቅባት ጸጋ ነት፡፡»

:23

ፈርዖን አለ «(ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው»

:24

(ሙሳ) «የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤» አለው፡፡

:25

(ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች «አትሰሙምን» አለ፡፡

:26

(ሙሳ) «ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው» አለው፡፡

:27

(ፈርዖን)

:28

(ሙሳ) «የምሥራቅና የምዕራብ በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ ታውቁ እንደኾናችሁ (እመኑበት)» አለው፡፡

:29

(ፈርዖን) «ከእኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ» አለ፡፡

:30

(ሙሳ) «በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ» አለው፡፡

:31

«እንግዲያውስ ከእውነተኞች እንደኾንክ (አስረጁን) አምጣው» አለ፡፡

:32

በትሩንም ጣለ፡፡ እርሷም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች፡፡

:33

እጁንም አወጣ፡፡ ወዲያውም እርሷ ለተመልካቾች (የምታበራ) ነጭ ኾነች፡፡

:34

(ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት «ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው» አለ፡፡

:35

«ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ» (አላቸው)፡፡

:36

አሉት «እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን ላክ፡፡

:37

«በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና፡፡»

:38

ድግምተኞቹም በታወቀ ቀን ቀጠሮ ተሰበሰቡ፡፡

:39

ለሰዎቹም «እናንተ ተሰብስባችኋልን» ተባለ፡፡

:40

«ድግምተኞቹን እነሱ አሸናፊዎች ቢኾኑ እንከተል ዘንድ» (ተባለ)፡፡

:41

«ድግምተኞቹም በመጡ ጊዜ ለፈርዖን እኛ አሸናፊዎች ብንሆን ለእኛ በእርግጥ ዋጋ አለን» አሉት፡፡

:42

«አዎን፤ እናንተም ያን ጊዜ ከባለሟሎቹ ትኾናላችሁ» አላቸው፡፡

:43

ሙሳ «ለእነርሱ እናንተ የምትጥሉትን ጣሉ» አላቸው፡፡

:44

ገመዶቻቸውንና በትሮቻቸውንም ጣሉ፡፡ «በፈርዖንም ክብር ይኹንብን፡፡ እኛ በእርግጥ አሸናፊዎቹ እኛ ነን» አሉ፡፡

:45

ሙሳም በትሩን ጣለ፡፡ ወዲያውም እርሷ የሚያስመስሉትን ሁሉ ትውጣለች፡፡

:46

ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡

:47

(እነሱም) አሉ «በዓለማት ጌታ አመንን፡፡

:48

«በሙሳና በሃሩን ጌታ፡፡»

:49

(ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ታላቃችሁ ነው፡፡ ወደፊትም (የሚያገኛችሁን) በእርግጥ ታውቃላችሁ፡፡ እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን (ቀኝና ግራን) በማናጋት እቆረርጣለሁ፡፡ ሁላችሁንም እሰቅላችኋለሁም» አለ፡፡

:50

(እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን፡፡

:51

«እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡»

:52

ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፡፡ እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና» ስንል ላክን፡፡

:53

ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ፡፡

:54

«እነዚህ ጥቂቶች ጭፈሮች ናቸው፡፡

:55

«እነርሱም ለእኛ አስቆጪዎች ናቸው፡፡

:56

«እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤» (አለ)፡፡

:57

አወጣናቸውም፡፡ ከአትክልቶችና ከምንጮች፡፡

:58

ከድልቦችም ከመልካም መቀመጫዎችም፡፡

:59

እንደዚሁ ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም፡፡

:60

ፀሐይዋ ስትወጣም ተከተሉዋቸው፡፡

:61

ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ የሙሳ ጓዶች «እኛ(የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን» አሉ፡፡

:62

(ሙሳ) «ተዉዉ! ጌታዬ ከእኔ ጋር ነው፡፡ በእርግጥ ይመራኛል» አለ፡፡

:63

ወደ ሙሳም «ባሕሩን በበትርህ ምታው» ስንል ላክንበት፡፡ (መታውና) ተከፈለም፡፡ ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ፡፡

:64

እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን፡፡

:65

ሙሳንም ከእርሱ ገር ያሉትንም ሰዎች ሁሉንም አዳን፡፡

:66

ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡

:67

በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡

:68

ጌታህም እርሱ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:69

በእነሱም (በሕዝቦችህ) ላይ የኢብራሂምን ወሬ አንብብላቸው፡፡

:70

ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ምንን ትግገዛላችሁ» ባለ ጊዜ፡፡

:71

«ጣዖታትን እንገዛለን፤ እርሷንም በመገዛት ላይ እንቆያለን» አሉ፡፡

:72

(እርሱም) አለ «በጠራችኋቸው ጊዜ ይሰሟችኋልን

:73

«ወይስ ይጠቅሟችኋልን ወይስ ይጎዷችኋልን»

:74

«የለም! አባቶቻችን እንደዚሁ ሲሠሩ አገኘን» አሉት፡፡

:75

«ትግገዙት የነበራችሁትን አስተዋላችሁን

:76

«እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም (የተግገዛችሁትን)፡፡»

:77

«እነሱም (ጣዖቶቹ) ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡

:78

«(እርሱ) ያ የፈጠረኝ ነው፡፡ እርሱም ይመራኛል፡፡

:79

«ያም እርሱ የሚያበላኝና የሚያጠጣኝ ነው፡፡

:80

«በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡

:81

«ያም የሚገድለኝ ከዚያም ሕያው የሚያደርገኝ ነው፡፡

:82

ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው፡፡

:83

ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ስጠኝ! በደጋጎቹም ሰዎች አስጠጋኝ፡፡

:84

በኋለኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ለእኔ መልካም ዝናን አድርግልኝ፡፡

:85

የጸጋይቱን ገነት ከሚወርሱትም አድርገኝ፡፡

:86

ለአባቴም ማር፡፡ እርሱ ከተሳሳቱት ነበረና፡፡

:87

በሚቀሰቀሱበት ቀንም አታዋርደኝ፡፡

:88

ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፡፡

:89

ወደ አላህ በንጹህ ልብ የመጣ ሰው ቢኾን እንጅ፡፡»

:90

ገነትም ለፈሪዎች በምትቀረብበት (ቀን)፡፡

:91

ገሀነምም ለጠመሞች በምትገለጽበት (ቀን)፡፡

:92

ለእነሱም በሚባል ቀን «ትግገዟቸው የነበራችሁት የት ናቸው»

:93

«ከአላህ ሌላ ሲኾኑ ይረዱዋችኋልን ወይስ (ለራሳቸው) ይርረዳሉን»

:94

በውስጧም እነሱና ጠማሞቹ በፊቶቻቸው ተጥለው ይንከባለላሉ፡፡

:95

የሰይጣንም ሰራዊቶች መላውም (ይጣላሉ)፡፡

:96

እነርሱም በእርሷ ውስጥ የሚከራከሩ ኾነው ይላሉ፡-

:97

በአላህ እንምላለን፤ እኛ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነበርን፡፡

:98

(ጣዖቶቹን) በዓለማት ጌታ ባስተካከልናችሁ ጊዜ፡፡

:99

አመጸኞቹም እንጅ ሌላ አላሳሳተንም፡፡

:100

ከአማላጆችም ለእኛ ምንም የለንም፡፡

:101

አዛኝ ወዳጂም (የለንም)፡፡

:102

ለእኛም አንዲት ጊዜ መመለስ በኖረችንና ከአማኞቹ በኾን እንመኛለን (ይላሉ)፡፡

:103

በዚህ ውስጥ አስደናቂ ግሳጼ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡

:104

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:105

የኑሕ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባበሉ፡፡

:106

ወንድማቸው ኑሕ ለእነሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን

:107

«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡

:108

«አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡

:109

«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡

:110

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡»

:111

(እነርሱም) «ወራዶቹ የተከተሉህ ኾነህ ለአንተ እናምናለን» አሉት፡፡

:112

(እርሱም) አላቸው «ይሠሩት በነበሩት ነገር ምን ዕውቀት አለኝ፡፡

:113

«ምርመራቸው በጌታዬ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ ብታውቁ ኖሮ (ይህንን ትርረዱ ነበር)፡፡

:114

«እኔም አማኞችን አባራሪ አይደለሁም፡፡

:115

«እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም፡፡»

:116

«ኑሕ ሆይ! (ከምትለው) ባትከለከል በእርግጥ ከሚወገሩት ትኾናለህ» አሉት፡፡

:117

(እርሱም) አለ «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ አስተባበሉኝ፡፡

:118

«በእኔና በእነርሱም መካከል (ተገቢ) ፍርድን ፍረድ፡፡ አድነኝም፡፡ ከእኔ ጋር ያሉትንም ምእምናን፡፡»

:119

እርሱንም ከእርሱ ጋር ያለውንም ሁሉ በተመላው መርከብ ውስጥ አዳን፡፡

:120

ከዚያም በኋላ ቀሪዎቹን አሰጠምን፡፡

:121

በዚህ ውስጥ ታላቅ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡

:122

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:123

ዓድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡

:124

ወንድማቸው ሁድ ለነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን

:125

«እኔ ለናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡

:126

«አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡

:127

«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡

:128

«የምትጫወቱ ኾናችሁ በከፍተኛ ስፍራ ሁሉ ላይ ምልክትን ትገነባላችሁን

:129

«የውሃ ማጠራቀሚያዎችንና ሕንፃዎችንም ዘላለም መኖርን የምትከጅሉ ኾናችሁ ትሠራላችሁን

:130

«በቀጣችሁም ጊዜ ጨካኞች ኾናችሁ ትቀጣላችሁን

:131

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡

:132

«ያንንም በምታውቁት (ጸጋ) ያጣቀማችሁን ፍሩ፡፡

:133

«በእንስሳዎችና በልጆች ያጣቀማችሁን፡፡

:134

«በአትክልቶችና በምንጮችም፡፡

:135

«እኔ በእናንተ ላይ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁና፡፡»

:136

(እነርሱም) አሉ «ብትገስጽም ወይም ከገሳጮቹ ባትኾንም በእኛ ላይ እኩል ነው፤ (ያለንበትን አንለቅም)፡፡

:137

«ይህ የፊተኞቹ ሰዎች ፀባይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡

:138

«እኛም የምንቅቀጣ አይደለንም» (አሉ)፡፡

:139

አስተባበሉትም፡፡ አጠፋናቸውም፡፡ በዚህም ውስጥ እርግጠኛ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡

:140

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:141

ሰሙድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡

:142

ወንድማቸው ሷሊህ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን

:143

«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡

:144

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡

:145

«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡

:146

«በዚያ እዚህ ባለው (ጸጋ) ውስጥ የረካችሁ ኾናችሁ ትተዋላችሁን

:147

«በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ፡፡

:148

«በአዝመራዎችም ፍሬዋ የበሰለ በኾነች ዘንባባም፤ (ውስጥ ትተዋላችሁን)

:149

«ብልሆች ኾናችሁ ከጋራዎች ቤቶችንም ትጠርባላችሁ፡፡

:150

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡

:151

«የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፡፡

:152

«የእነዚያን በምድር ላይ የሚያጠፉትንና የማያበጁትን፡፡»

:153

(እነሱም) አሉ «አንተ በብዙ ከተደገመባቸው ሰዎች ብቻ ነህ፡፡

:154

«አንተ ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ ከእውነተኞቹም እንደኾንክ ተዓምርን አምጣ፡፡»

:155

(እርሱም) አለ «ይህች ግመል ናት፡፡ ለእርሷ የመጠጥ ፋንታ አላት፡፡ ለእናንተም የታወቀ ቀን ፋንታ አላችሁ፡፡

:156

«በክፉም አትንኳት፡፡ የታላቅ ቀን ቅጣት ይይዛችኋልና፡፡»

:157

ወጓትም፡፡ ወዲያውም ተጸጻቾች ኾነው አነጉ፡፡

:158

ቅጣቱም ያዛቸው፡፡ በዚህም ውስጥ ግሳፄ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡

:159

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:160

የሉጥ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባባሉ፡፡

:161

ወንድማቸው ሉጥ ለእነርሱ ባለ ጊዜ «አትጠነቀቁምን

:162

«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡

:163

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡

:164

«በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡

:165

«ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን

:166

«ከሚስቶቻችሁም ጌታችሁ ለናንተ የፈጠረላችሁን ትተዋላችሁን በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦ ናችሁ፡፡»

:167

(እነርሱም) አሉ «ሉጥ ሆይ! ባትከለከል በእርግጥ (ከአገር) ከሚወጡት ትኾናለህ፡፡»

:168

(እርሱም) አለ «እኔ ሥራችሁን ከሚጠሉት ሰዎች ነኝ፡፡

:169

«ጌታዬ ሆይ! እኔንም ቤተሰቦቼንም ከሚሠሩት ሥራ (ቅጣት) አድነን፡፡»

:170

እርሱንም ቤተሰቦቹንም በጠቅላላ አዳንናቸው፡፡

:171

በቀሪዎቹ ውስጥ የኾነች አሮጊት ብቻ ስትቀር (እርሷ ጠፋች)፡፡

:172

ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡

:173

በእነሱም ላይ (የድንጋይን) ዝናምን አዘነምንባቸው፡፡ የተስፈራሪዎቹም ዝናም (ምንኛ) ከፋ፡፡

:174

በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡

:175

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:176

የአይከት ሰዎች መልክተኞችን አስተባበሉ፤

:177

ሹዕይብ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን

:178

«እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡

:179

«አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡

:180

«በርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡

:181

«ስፍርን ሙሉ፡፡ ከአጉዳዮቹም አትኹኑ፡፡

:182

«በትክክለኛ ሚዛንም መዝኑ፡፡

:183

«ሰዎችንም ነገሮቻቸውን አታጉድሉባቸው፡፡ በምድርም ላይ አጥፊዎች ኾናችሁ አታበላሹ፡፡

:184

«ያንንም የፈጠራችሁን የቀድሞዎቹንም ፍጡሮች (የፈጠረውን) ፍሩ፡፡»

:185

አሉ «አንተ በብዛት ከተደገመባቸው ሰዎች ነህ፡፡

:186

«አንተም ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ እነሆ ከውሸታሞች ነህ ብለን እንጠረጥርሃለን፡፡

:187

«ከእውነተኞቹም እንደኾንክ በእኛ ላይ ከሰማይ ቁራጭን ጣልብን፡፡»

:188

«ጌታዬ የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፤» አላቸው፡፡

:189

አስተባበሉትም፡፡ የጥላይቷ ቀን ቅጣትም ያዛቸው፡፡ እርሱ የከባድ ቀን ቅጣት ነበርና፡፡

:190

በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእምናን አልነበሩም፡፡

:191

ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡

:192

እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡

:193

እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤

:194

ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡

:195

ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡

:196

እርሱም (ቁርኣን) በቀድሞዎቹ መጻሐፍት ውስጥ (የተወሳ ነው)፡፡

:197

የእስራኤል ልጆች ሊቃውንት የሚያውቁት መኾኑ ለእነርሱ (ለመካ ከሓዲዎች) ምልክት አይኾናቸውምን

:198

ከአዕጀሞች ባንዱ ላይ ባወረድነውም ኖሮ፤

:199

በእነርሱ ላይ ባነበበውም በእርሱ አማኞች አይኾኑም ነበር፡፡

:200

እንደዚሁ (ማስተባበልን) በተንኮለኞች ልቦች ውስጥ አስገባነው፡፡

:201

አሳማሚ ቅጣትን እስከሚያዩ ድረስ በእርሱ አያምኑም፡፡

:202

እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ (ቅጣቱ) ድንገት እስከሚመጣባቸውም ድረስ (አያምኑም)፡፡

:203

(በመጣባቸው ጊዜ) «እኛ የምንቆይ ነን» እስከሚሉም (አያምኑም)፡፡

:204

በቅጣታችን ያቻኩላሉን

:205

አየህን ብዙ ዓመታትን ብናጣቅማቸው፤

:206

ከዚያም ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ቢመጣባቸው፤

:207

ይጣቀሙበት የነበሩት ሁሉ ከእነሱ ምንም አያብቃቃቸውም፡፡

:208

አንዲትንም ከተማ ለእርሷ አስፈራሪዎች ያሏት (እና ያስተባበለች) ኾና እንጅ አላጠፋንም፡፡

:209

(ይህች) ግሳፄ ናት፡፡ በዳዮችም አልነበርንም፡፡

:210

ሰይጣናትም እርሱን (ቁርኣንን) አላወረዱትም፡፡

:211

ለእነርሱም አይገባቸውም፤ አይችሉምም፡፡

:212

እነርሱ (የመላእክትን ንግግር) ከመስማት ተከለከሉ ናቸው፡፡

:213

ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፤ ከሚቀጡት ትኾናለህና፡፡

:214

ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ፡፡

:215

ከምእምናንም ለተከተሉህ ሰዎች ክንፍህን ዝቅ አድርግ፤ (ልዝብ ኹን)፡፡

:216

«እንቢ» ቢሉህም «እኔ ከምትሠሩት ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡

:217

አሸናፊ አዛኝ በኾነው (ጌታህ) ላይም ተጠጋ፡፡

:218

በዚያ ለሶላት በምትቆም ጊዜ በሚያይህ፡፡

:219

በሰጋጆች ውስጥ መዘዋወርህንም (በሚያየው ጌታህ ላይ ተጠጋ)፡፡

:220

እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡

:221

ሰይጣናት በማን ላይ እንደሚወርዱ ልንገራችሁን

:222

በውሸታም ኀጢአተኛ ሁሉ ላይ ይወርዳሉ፡፡

:223

የሰሙትን (ወደ ጠንቋዮች) ይጥላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም ውሸታሞች ናቸው፡፡

:224

ባለ ቅኔዎችንም ጠማማዎቹ ይከተሉዋቸዋል፡፡

:225

እነርሱ በ(ንግግር) ሸለቆ ሁሉ የሚዋልሉ መኾናቸውን አታይምን

:226

እነሱም የማይሠሩትን ነገር የሚናገሩ መኾናቸውን (አታይምን)፤

:227

እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ አላህንም በብዛት ያወሱ ከተበደሉም በኋላ (በቅኔ) የተከላከሉ ሲቀሩ፤ (እነርሱ አይወቀሱም)፡፡ እነዚያም የበደሉ (ከሞቱ በኋላ) እንዴት ያለን መመለስ እንደሚመለሱ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡