ሁሉም የእስልምና ቤተ መጻሕፍት

21 - The Prophets - Al-'Anbyā

:1

ለሰዎች እነርሱ በዝንጋቴ ውስጥ (መሰናዳትን) የተው ኾነው ሳሉ ምርመራቸው ቀረበ፡፡

:2

ከጌታቸው አዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፡፡ እነሱ የሚያላግጡ ሆነው የሚያደምጡት ቢሆኑ እንጂ፡፡

:3

ልቦቻቸው ዝንጉዎች ኾነው (የሚያዳምጡት ቢኾኑ እንጅ)፡፡ እነዚያም የበደሉት ሰዎች መንሾካሾክን ደበቁ፡፡ «ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ ነውን እናንተም የምታዩ ስትኾኑ ድግምትን ለመቀበል ትመጣላችሁን» (አሉ)፡፡

:4

(ሙሐመድም) «ጌታዬ ቃልን ሁሉ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለ ሲኾን ያውቃል እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው» አለ፡፡

:5

«በእውነቱ (ቁርኣኑ) የሕልሞች ቅዠቶች ነው፡፡ ይልቁንም ቀጠፈው እንዲያውም እርሱ ቅኔን ገጣሚ ነው፡፡ የቀድሞዎቹም እንደተላኩ (መልክተኛ ከኾነ) በተዓምር ይምጣብን» አሉ፡፡

:6

ከእነሱ በፊት ያጠፋናት ከተማ አላመነችም፡፡ ታዲያ እነሱ ያምናሉን

:7

ከአንተም በፊት ወደእነሱ የምናወርድላቸው የኾነን ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ፡፡

:8

ምግብን የማይበሉ አካልም አላደረግናቸውም፡፡ ዘውታሪዎችም አልነበሩም፡፡

:9

ከዚያም ቀጠሮን ሞላንላቸው፡፡ አዳንናቸውም፡፡ የምንሻውንም ሰው (አዳን)፡፡ ወሰን አላፊዎቹንም አጠፋን፡፡

:10

ክብራችሁ በውስጡ ያለበትን መጽሐፍ ወደእናንተ በእርግጥ አወረድን፡፡ አታውቁምን

:11

በዳይም ከነበረች ከተማ ያጠፋናትና ከኋላዋም ሌሎችን ሕዝቦች ያስገኘነው ብዙ ናት፡፡

:12

ቅጣታችንም በተሰማቸው ጊዜ እነርሱ ወዲያውኑ ከእርሷ (ለመሸሽ) ይገሠግሣሉ፡፡

:13

አትገሥግሡ፤ ትለመኑም ይኾናልና፡፡ በእርሱ ወደ ተቀማጠላችሁበት ጸጋ ወደ መኖሪያዎቻችሁም ተመለሱ (ይባላሉ)፡፡

:14

«ዋ ጥፋታችን! እኛ በእርግጥ በዳዮች ነበርን» ይላሉ፡፡

:15

የታጨዱ ሬሳዎችም እስካደረግናቸው ድረስ ይህቺ ጠሪያቸው ከመኾን አልተወገደችም፡፡

:16

ሰማይንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ ቀላጆች ኾነን አልፈጠርንም፡፡

:17

መጫወቻን (ሚስትና ልጅን) ልንይዝ በሻን ኖሮ ከእኛ ዘንድ በያዝነው ነበር፡፡ (ግን) ሠሪዎች አይደለንም፡፡

:18

በእርግጥ እውነትን በውሸት ላይ እንጥላለን፡፡ አንጎሉን ያፈርሰዋልም፡፡ ወዲያውም እርሱ ጠፊ ነው፡፡ ለእናንተም ከዚያ (ሚስትና ልጅ አለው በማለት) ከምትመጥኑት ነገር ብርቱ ቅጣት አላችሁ፤ (ወዮላችሁ)፡፡

:19

በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ እርሱ ዘንድ ያሉትም (መላእክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፡፡ አይሰለቹምም፡፡

:20

በሌሊትና በቀንም ያጠሩታል፤ አያርፉም፡፡

:21

ይልቁንም ከምድር የኾኑን እነርሱ ሙታንን የሚያስነሱን አማልክት ያዙን (የለም)፡፡

:22

በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፡፡ የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡

:23

ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ (ፍጥረቶቹ) ግን ይጠየቃሉ፡፡

:24

ይልቁንም ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙን «አስረጃችሁን አምጡ፡፡ ይህ (ቁርኣን) እኔ ዘንድ ያለው ሕዝብ መገሰጫ ከእኔ በፊትም የነበሩት ሕዝቦች መገሰጫ ነው» በላቸው፡፡ በውነቱ አብዛኞቻቸው እውነቱን አያውቁም፡፡ ስለዚህ እነሱ እምቢተኞች ናቸው፡፡

:25

ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡

:26

«አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ» አሉ፡፡ ጥራት ተገባው፡፡ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው፡፡

:27

በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)፡፡ እነርሱም በትእዛዙ ይሠራሉ፡፡

:28

በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም፡፡ እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው፡፡

:29

ከእነሱም «እኔ ከእርሱ ሌላ አምላክ ነኝ» የሚል ያንን ገሀነምን እንመነዳዋለን፡፡ እንደዚሁ በዳዮችን እንመነዳለን፡፡

:30

እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መኾናችንን አያውቁምን ሕያው የኾነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፡፡ አያምኑምን

:31

በምድርም ውስጥ በእነሱ እንዳታረገርግ ጋራዎችን አደረግን፡፡ ይመሩም ዘንድ በእርሷ ውስጥ ሰፋፊ መንገዶችን አደረግን፡፡

:32

ሰማይንም (ከመውደቅ) የተጠበቀ ጣራ አደረግን፡፡ እነርሱም ከተዓምራቶቿ ዘንጊዎች ናቸው፡፡

:33

እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፡፡ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡

:34

(ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊት ለማንም ሰው ዘለዓለም መኖርን አላደረግንም፡፡ ታዲያ ብትሞት እነሱ ዘውታሪዎች ናቸውን

:35

ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፡፡ ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንሞክራችኋለን፡፡ ወደኛም ትመለሳላችሁ፡፡

:36

እነዚያም የካዱት ሰዎች ባዩህ ጊዜ መሳለቂያ አድርገው እንጂ አይይዙህም፡፡ እነሱ በአልረሕማን መወሳት እነርሱ ከሓዲዎች ሲሆኑ «ያ አማልክቶቻችሁን (በክፉ) የሚያነሳው ይህ ነውን» (ይላሉ)፡፡

:37

ሰው ቸኳይ ሆኖ ተፈጠረ፡፡ ተዓምራቶቼን በእርግጥ አሳያችኋለሁና አታቻኩሉኝ፡፡

:38

«ይህ ቀጠሮም መቼ ነው እውነተኞች ከኾናችሁ (አምጡት)» ይላሉ፡፡

:39

እነዚያ የካዱት ከፊቶቻቸውና ከጀርባዎቻቸው ላይ እሳትን የማይከለክሉበትን እነሱም የማይረዳዱበትን ጊዜ ቢያውቁ ኖሮ (ይህንን አይሉም ነበር)፡፡

:40

ይልቁንም (ሰዓቲቱ) በድንገት ትመጣቸዋለች፤ ታዋልላቸዋለችም፡፡ መመለሷንም አይችሉም፡፡ እነሱም አይቆዩም፡፡

:41

ከአንተ በፊትም የነበሩት መልክተኞች በእርግጥ ተቀለደባቸው፡፡ በእነዚያም ከእነሱ ይቀልዱ በነበሩት በርሱ ይሳለቁበት የነበሩት (ቅጣት) ሰፈረባቸው፡፡

:42

«ከአልረሕማን (ቅጣት) በሌሊትና በቀን የሚጠብቃችሁ ማነው» በላቸው፡፡ በእውነቱ እነሱ ከጌታቸው ግሳጼ (ከቁርአን) ዘንጊዎች ናቸው፡፡

:43

ለእነሱ ከእኛ ሌላ የምትከላከልላቸው አማልክት አለቻቸውን ነፍሶቻቸውን መርዳትን አይችሉም፡፡ እነርሱም (ከሓዲዎቹ) ከእኛ አይጠበቁም፡፡

:44

በእውነት እነዚህንና አባቶቻቸውን በእነሱ ላይ ዕድሜ እስከ ረዘመባቸው ድረስ አጣቀምናቸው፡፡ (ተታለሉም)፡፡ እኛ ምድርን ከጫፎችዋ የምናጎላት ኾነን ስንመጣባት አያዩምን እነሱ አሸናፊዎች ናቸውን

:45

«የማስፈራራችሁ በተወረደልኝ ብቻ ነው፡፡ ግን ደንቆሮዎች በሚስፈራሩ ጊዜ ጥሪን አይሰሙም» በላቸው፡፡

:46

ከጌታህ ቅጣትም ወላፈን ብትነካቸው «ዋ ጥፋታችን! እኛ በዳዮች ነበርን» ይላሉ፡፡

:47

በትንሣኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን፡፡ ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፡፡ (ሥራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን፡፡ ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ፡፡

:48

ለሙሳና ለሃሩንም እውነትንና ውሸትን የሚለይን ብርሃንንም ለጥንቁቆችም መገሰጫን በእርግጥ ሰጠናቸው፡፡

:49

ለእነዚያ ጌታቸውን በሩቅ ለሚፈሩት እነሱም ከሰዓቲቱ ተጨናቂዎች ለኾኑ (መገሰጫን ሰጠን)፡፡

:50

ይህም (ቁርኣን) ያወረድነው የኾነ ብሩክ መገሰጫ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ ለእርሱ ከሓዲዎች ናችሁን

:51

ለኢብራሂምም ከዚያ በፊት ቅን መንገዱን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እኛም በእርሱ (ተገቢነት) ዐዋቂዎች ነበርን፡፡

:52

ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ይህቺ ቅርጻ ቅርጽ ያቺ እናንተ ለእርሷ ተገዢዎች የኾናችሁት ምንድን ናት» ባለ ጊዜ (መራነው)፡፡

:53

«አባቶቻችንን ለእርሷ ተገዢዎች ኾነው አገኘን» አሉት፡፡

:54

«እናንተም አባቶቻችሁም በእርግጥ በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበራችሁ» አላቸው፡፡

:55

«በምሩ መጣህልን ወይንስ አንተ ከሚቀልዱት ነህ» አሉት፡፡

:56

«አይደለም ጌታችሁ የሰማያትና የምድር ጌታ ያ የፈጠራቸው ነው፡፡ እኔም በዚህ ላይ ከመስካሪዎቹ ነኝ» አለ፡፡

:57

«በአላህም እምላለሁ ዟሪዎች ኾናችሁ ከሄዳችሁ በኋላ ጣዖቶቻችሁን ተንኮል እሠራባቸዋለሁ» (አለ)፡፡

:58

(ዘወር ሲሉ) ስብርብሮችም አደረጋቸው፡፡ ለእነሱ የኾነ አንድ ታላቅ (ጣዖት) ብቻ ሲቀር ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ (እርሱን ተወው)፡፡

:59

«በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራ ማነው እርሱ በእርግጥ ከበደለኞች ነው» አሉ፡፡

:60

«ኢብራሂም የሚባል ጎበዝ (በመጥፎ) ሲያነሳቸው ሰምተናል» ተባባሉ፡፡

:61

«ይመሰክሩበት ዘንድ በሰዎቹ ዓይን (ፊት) ላይ አምጡት» አሉ፡፡

:62

«ኢብራሂም ሆይ! በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራህ አንተ ነህን» አሉት፡፡

:63

«አይደለም ይህ ታላቃቸው ሠራው፡፡ ይናገሩም እንደ ኾነ ጠይቋቸው» አለ፡፡

:64

ወደ ነፍሶቻቸውም ተመለሱ፡፡ «እናንተ (በመጠየቃችሁ) በዳዮቹ እናንተው ናችሁም» ተባባሉ፡፡

:65

ከዚያም በራሶቻቸው ላይ ተገለበጡ፡፡ «እነዚህ የሚናገሩ አለመኾናቸውን በእርግጥ ዐውቀሃል፤» (አሉ)፡፡

:66

«ታዲያ ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትገዛላችሁን» አላቸው፡፡

:67

«ፎህ! ለእናንተ ከአላህ ሌላ ለምትገዙትም ነገር፤ አታውቁምን» (አለ)፡፡

:68

«ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት፡፡ አማልክቶቻችሁንም እርዱ» አሉ፡፡ (በእሳት ላይ ጣሉትም)፡፡

:69

«እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ ሰላምም ሁኚ» አልን፡፡

:70

በእርሱም ተንኮልን አሰቡ፡፡ በጣም ከሳሪዎችም አደረግናቸው፡፡

:71

እርሱንና ሉጥንም ወደዚያች፤ በውስጧ ለዓለማት በረከትን ወደ አደረግንባት ምድር (በመውሰድ) አዳን፡፡

:72

ለእርሱም ኢስሐቅን ያዕቆብንም ተጨማሪ አድርገን ሰጠነው፡፡ ሁሉንም መልካሞች አደረግን፡፤

:73

በትዕዛዛችንም ወደ በጎ ሥራ የሚመሩ መሪዎች አደረግናቸው፡፡ ወደእነሱም መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አወረድን፡፡ ለእኛ ተገዢዎችም ነበሩ፡፡

:74

ሉጥንም ፍርድንና ዕውቀትን ሰጠነው፡፡ ከዚያችም መጥፎ ሥራዎችን ትሠራ ከነበረችው ከተማ አዳንነው፡፡ እነሱ ክፉ ሰዎች አመጸኞች ነበሩና፡፡

:75

በችሮታችንም ውስጥ አገባነው፡፡ እርሱ ከመልካሞቹ ነውና፡፡

:76

ኑሕንም ከዚያ በፊት (ጌታውን) በጠራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ለእርሱም (ጥሪውን) ተቀበልነው፡፡ እርሱንም ቤተሰቦቹንም ከከባድ ጭንቅ አዳን፡፡

:77

ከነዚያም በታምራቶቻችን ከአስተባበሉት ሕዝቦች (ተንኮል) ጠበቅነው፡፡ እነሱ ክፉ ሕዝቦች አመጸኞች ነበሩና፡፡ ሁሉንም አሰጠምናቸውም፡፡

:78

ዳውድንና ሱለይማንንም በአዝመራው ነገር በሚፈርዱ ጊዜ የሕዝቦቹ ፍየሎች ሌሊት በርሱ ውስጥ በተሰማሩ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ፍርዳቸውንም ዐዋቂዎች ነበርን፡፡

:79

ለሱለይማንም (ትክክለኛይቱን ፍርድ) አሳወቅናት፡፡ ለሁሉም ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠን፡፡ ተራራዎችን ከዳውድ ጋር የሚያወድሱ ሲኾኑ ገራን፡፡ አእዋፍንም (እንደዚሁ ገራን)፡፡ ሠሪዎችም ነበርን፡፡

:80

የብረት ልብስንም ሥራ ለእናንተ ከጦራችሁ ትጠብቃችሁ ዘንድ አስተማርነው፡፡ እናንተ አመስጋኞች ናችሁን

:81

ለሱለይማንም ነፋስን በኀይል የምትነፍስ በትዕዛዙ ወደዚያች በእርሷ ውስጥ በረከትን ወደ አደረግንባት ምድር (ወደ ሻም) የምትፈስ ስትኾን (ገራንለት)፡፡ በነገሩ ሁሉም ዐዋቂዎች ነበርን፡፡

:82

ከሰይጣናትም ለእርሱ (ሉልን ለማውጣት) የሚጠልሙንና ከዚያም ሌላ ያለን ሥራ የሚሠሩን (ገራንለት)፡፡ ለእነሱም ተጠባባቂዎች ነበርን፡፡

:83

አዩብንም (ኢዮብን) ጌታውን «እኔ መከራ አገኘኝ አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ» ሲል በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:84

ለእርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ከጉዳትም በእርሱ ላይ የነበረውን ሁሉ አስወገድን፡፡ ቤተሰቦቹንም ከእነሱም ጋር መሰላቸውን ከእኛ ዘንድ ለችሮታና ለተገዢዎች ለማስገንዘብ ሰጠነው፡፡

:85

ኢስማዒልንም ኢድሪስንም ዙልኪፍልንም (አስታውስ)፡፡ ሁሉም ከታጋሾቹ ናቸው፡፡

:86

ከችሮታችንም ውስጥ አገባናቸው፡፡ እነሱ ከመልካሞቹ ናቸውና፡፡

:87

የዓሳውንም ባለቤት ተቆጥቶ በኼደ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በእርሱም ላይ ፈጽሞ የማንፈርድበት መኾናችንን ጠረጠረ፡፡ (ዓሳም ዋጠው)፡፡ በጨለማዎችም ውስጥ ኾኖ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ጥራት ይገባህ፡፡ እኔ በእርግጥ ከበዳዮቹ ነበርኩ በማለት ተጣራ፡፡

:88

ለርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ከጭንቅም አዳነው፡፡ እንደዚሁም ምእመናንን እናድናለን፡፡

:89

ዘከሪያንም «ጌታዬ ሆይ! ብቻዬን አትተወኝ፡፡ አንተም ከወራሾች ሁሉ በላጭ ነህ ሲል» ጌታውን በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

:90

ለእርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ለእርሱም የሕያን ሰጠነው፡፡ ለእርሱም ሚስቱን አበጀንለት፡፡ እነርሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም ነበሩ፡፡ ለእኛ ተዋራጆችም ነበሩ፡፡

:91

ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን እርሷንም ልጅዋንም (እንደዚሁ) ለዓለማት ተዓምር ያደረግናትን (መርየምን አስታውስ)፡፡

:92

ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ፡፡

:93

በሃይማኖታቸውም ነገር በመካከላቸው ተለያዩ፡፡ ሁሉም ወደኛ ተመላሾች ናቸው፡፡

:94

እርሱ ያመነ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች ማንኛውንም የሚሠራም ሰው፤ ምንዳውን አይነፈግም፡፡ እኛም ለእርሱ መዝጋቢዎች ነን፡፡

:95

ባጠፋናትም ከተማ ላይ እነሱ (ወደኛ) የማይመለሱ መኾናቸው እብለት ነው፤ (ይመለሳሉ)፡፡

:96

የእጁጅና መእጁጅም እነርሱ ከየተረተሩ የሚንደረደሩ ሲኾኑ (ግድባቸው) በተከፈተች ጊዜ፥

:97

እውነተኛውም ቀጠሮ በቀረበ ጊዜ፥ ያን ጊዜ እነሆ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ዓይኖች ይፈጥጣሉ፡፡ «ዋ ጥፋታችን! ከዚህ (ቀን) በእርግጥ በዝንጋቴ ላይ ነበርን፤ በእውነትም በዳዮች ነበርን» (ይላሉ)፡፡

:98

እናንተ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውም (ጣዖታት) የገሀነም ማገዶዎች ናችሁ፡፡ እናንተ ለእርሷ ወራጆች ናችሁ፡፡

:99

እነዚህ (ጣዖታት) አማልክት በነበሩ ኖሮ አይገቧዋትም ነበር፡፡ ግን ሁሉም በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡

:100

ለእነርሱ በእርሷ ውስጥ መንሰቅሰቅ አላቸው፡፡ እነርሱም በውስጧ (ምንንም) አይሰሙም፡፡

:101

እነዚያ ከእኛ መልካሟ ቃል ለእነርሱ ያለፈችላቸው እነዚያ ከርሷ የተራቁ ናቸው፡፡

:102

ድምጽዋን አይሰሙም፡፡ እነርሱም ነፍሶቻቸው በሚሹት ነገር ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡

:103

ታላቁ ድንጋጤ አያስተክዛቸውም፡፡ መላእክትም ይህ ያ ትቀጠሩ የነበራችሁት ቀናችሁ ነው፤ እያሉ ይቀበሏቸዋል፡፡

:104

ለመጽሐፎች የኾኑ ገጾች እንደሚጠቀለሉ ሰማይን የምንጠቀልልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ የመጀመሪያን ፍጥረት እንደ ጀመርን እንመልሰዋለን፡፡ (መፈጸሙ) በእኛ ላይ የኾነን ቀጠሮ ቀጠርን፡፡ እኛ (የቀጠርነውን) ሠሪዎች ነን፡፡

:105

ምድንም መልካሞቹ ባሮቼ ይወርሷታል ማለትን ከመጽሐፉ (ከተጠበቀው ሰሌዳ) በኋላ በመጽሐፎቹ በእርግጥ ጽፈናል፡፡

:106

በዚህ (ቁርኣን) ውስጥ ለተገዢዎች ሕዝቦች በቂነት አልለ፡፡

:107

(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡

:108

«ያ ወደኔ የሚወረደው አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን» በላቸው፡፡

:109

እምቢም ቢሉ (በማወቅ) በእኩልነት ላይ ኾነን (የታዘዝኩትን) አስታውቅኋችሁ፡፡ «የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ ወይም ሩቅ መኾኑን አላውቅም፤» በላቸው፡፡

:110

እርሱ ከንግግር ጩኸትን ያውቃል፡፡ የምትደብቁትንም ሁሉ ያውቃል፡፡

:111

እርሱም (ቅጣትን ማቆየት) ምናልባት ለእናንተ ፈተናና እስከ ጊዜው መጠቃቀሚያ እንደሆነም አላውቅም፤ (በላቸው)፡፡

:112

«ጌታዬ ሆይ! በእውነት ፍረድ፤ ጌታችንም እጅግ በጣም ሩኅሩኅ በምትሉት ነገር ላይ መታገዣ ነው» አለ፡፡